የፍትሕ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርዓያ ስላሴ በገንዘብ ሚኒስቴር በተዘጋጀው እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም ዐቀፍ ተቋማት ተወካዮች በታደሙበት የውይይት መድረክ ተገኝተው የሽግግር ፍትሕ ትግበራ በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ አስመልከቶ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሯ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ እንዲሆን በመንግሥት ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ በፖሊሲ ዝግጅት ሂደት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ባቀረቡት ማብራሪያ በፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ዙሪያ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ከ80 በላይ የሚሆኑ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰው በውይይት ሂደቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች በሰነዱ ላይ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ማጽደቁን ተከትሎ የትግበራ ምዕራፉን የማስተባበር ኃላፊነት የተጣለበት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴርም በሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚከናወኑ ተግባራትን፣ ተግባራቱ የሚፈጸሙበትን የጊዜ ርዝመትና ፈጻሚ ባለ ድርሻ አካላትን በግልጽ ያስቀመጠ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሃና አክለው በፖሊሲው በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ስልቶችን የሚተገብሩ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያስችሉ የሕግ ረቂቆች መዘጋጀታቸውን ገልጸው በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች በኋላ ረቂቆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልከው እንደሚጸድቁ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሚቋቋሙ ተቋማት በሕግ የሚጣልባቸውን ኃላፊነት መወጣት በሚያስችላቸው ደረጃ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው በሚቋቋሙበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ፖሊሲው የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማውጣት፣ ቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምሕረት፣ ማካካሻ እና ተቋማዊ ማሻሻያ ላይ ያተኮረ ባለፉት አመታት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እልባት በመስጠት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የወጠነ መሆኑን አንስተዋል።
ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የተለያዩ መፍትሄዎችን ቀርጻ ለመተግበር ጥረት በምታደርግበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን አጽዕኖት ሰጥተው የገለጹት ክብርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሃና ለመድረኩ ታዳሚዎችም ባስተላፉት ጥሪም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲ ይሰፍን ዘንድ በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የልማት አጋሮች በሙሉ ከምን ጊዜውም በላይ ለሀገራችን ሰላም መረጋገጥ የአምሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡