የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከጀርመን ልማትር ድርጅት GIZ እና ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀውን እና በዘርፉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው በረቂቅ ሕግ ላይ የኤሌክትሮኒክ ምክክር ስርዓት መተግሪያ (E-consultation Portal)) የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ግንቦት 20/2017 ዓ.ም ይፋ ሆኗል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በመድረኩ እንደገለፁት በሕግ ዝግጅት ሂደት የፍትሕ ተቋማት የሕዝብና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ መስረት የሚገባቸው መሆኑን ጠቁመው ይህም የመንግሥትን አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት አንዱ ጥሩ ማሳያ እና የህገ-መንግሥት መርሆችን ተግባራዊ የማረጊያ አበይት መንገድ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
አክለውም በሕግ ዝግጅት ሂደት የሕዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ የህጎችን ጥራት ማሰጠበቅ ከማስቻሉም በላይ በአተገባበር ሂደትም የሕዝብ ቅቡልነት ያለው እና በአግባቡ የሚተገበር ሕግ እንዲሆን ያስችላል ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃርም ረቂቅ ህጎች ሲዘጋጁ ከህበረተሰቡ ግብዓት የሚሰባሰብበት ስርዓት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መዘጋጀቱ የሕዝብና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ እና ተዓማኒነቱን ከፍ የሚያደርገው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያስላሴ በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክ ምክክር ሥርዓቱ ከዜጎች፣ ከሕዝቡ፣ ልዩ ፍላጎት ካላቸው ዜጎች፣ እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች አስተያየቶችን ለመቀበል የሚያስችል አዲስ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰፊ ተደራሽነትን በመፍጠር ተጨማሪ ተሳትፎን የሚያበረታታና ግልጽነትን ለመፍጠር የሚያስችል፣ ፈጣን፣ ጊዜን በተሻለ ለመጠቀም የሚያስችል፣ የተሻለ ተሳትፎና ሃሳብ ለማግኘት የሚያስችልና በአነስተኛ ወጪ የሚከናወን ነው ብለዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ አያይዘውም ሥርዓቱ በክልል ደረጃም ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጎ የለማ በመሆኑ በሕግ አወጣጥ ሂደቱ የተሻለ ቅንጅትን የሚፈጥር፣ ወጥነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አይነተኛ የሕዝብና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማረጋገጫ እና መንግሥት እንደ ሀገር አሰራሩን በዲጂታል ሥርዓት ለመደገፍ እያደረገው ያለው ጥረት አንድ መገለጫ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በመድረኩ የጀርመን የልማት ድርጅት ተወካይ ዶ/ር አልቤርቶ ጎሜዝ ተገኝተው ባስተላፉት መልዕክት እንዲሁ ይህ የኤሌክትሮኒክ ምክክር ሥርዓት በአጠቃላይ የፍትሕ ስርዓቱን የሚያግዝና ጠቃሜተው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡