የፍትሕ ሚኒስቴር በፌደራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/12 ዙሪያ ከፌደራል ፍ\ቤት ዳኞች ጋር እያካሄደ ያለው የውይይት መድረክ ቀጥሏል::
በዛሬው መርሃ ግብርም በፌደራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ የክለሳ ስነ-ስርዓት ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ግኝት በፌደራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ መስታወት ደርሰህ ቀርቧል፤ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ የመንግሥትን አሠራር የምንሞግትበት፣ የምንገመግምበት እና የምንተችበት እድል የሰጠን በመሆኑ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ሲሉ ዐቃቤ ህጓ አሳስበዋል፡፡
ጥናቱ በፍትሕ ሚኒስቴር የተጠና ሲሆን የመመሪያ ክለሳ ዳኝነት ምክንያቶች፣ የአስተዳደር ውሳኔ ክለሳ አቤቱታ ምክንያቶች፣ በክለሳ ሂደት ላይ የታዩ ስርዓተ-ጥለቶች እና ዝንባሌዎች መዳሰሳቸው ተገልጿል፡፡
የዳሰሳ ጥናቱ ለሕግ አውጪው፣ ለሕግ አስፈፃሚው እንዲሁም ለፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ህጉን አተገባበር ለማዳበር ያስችላሉ ያላቸውን ዘርዘር ያሉ ምክረ ሃሳቦችን አካቶ ይዟል፡፡
ጥናቱ ባመላከታቸው ግኝቶች በርካታ ሀሳቦች የተንሸራሸሩ ሲሆን የፌደራል ዳኞቹ ላነሱት ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የፌደራል ከፍተኛ ፍ\ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ተህሊት ይመስል መድረኩን ሲዘጉ ባስተላለፉት መልዕክት የአስተዳደር ፍትሕን አስመልክቶ ለፍርድ ቤቶች በዘርፉ የዳበሩ አሰራሮችን ለማጎልበት የሚረዳ ዕድል የተፈጠረ መሆኑን ገልፀው ለዚህም ከሕግ፣ ከአረዳድና አተገባበር አንጻር የሚገጥሙ ውስንነቶችን መረዳት እንደሚጠቅም ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የዳኞችን ነጻነት በጠበቀ መልኩ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ቅንጅት በመፍጠር አዋጁ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ዘንድ ይህን መሰል መድረኮችን ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡
የውይይት መድረኩ ህዳር 14 እና 15 ቀን 2016 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡