የሕግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የደም ስር ነው፡፡ እንደ ሀገር ፈተና የሆነብንን የሕግ የበላይነት እና መልካም አስተዳደር የማስፈን ስራ በልዩ ትኩረት ለመሥራት እና የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት የአስተዳደር ፍትሕን ለማስፈን ከምንጊዜውም በላይ ህዝቡንና ህጉን ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመና “የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በዋናነት ከአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ትግበራና የአፈጻጸም ተግዳሮቶች ጋር የተያያዘ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ከሰኔ 19-20 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በተሳካ ሁኔታ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ ሰፋ ያሉ ውይይቶች ተደርገው የጋራ መግባባት ላይ በተደረሰባቸው ጉዳዮች እና መደምደሚያዎች መሠረት ዝርዝር የማስፈጸሚያ እቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ በተለይም ሁሉም የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት በአዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሠረት አገልግሎት እንዲሰጡ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፤ አዋጁ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በመደበኛ ፍርድ ቤት የቀረቡ የክለሳ ጥያቄዎችን በማጥናት (Case Study) ምከረ ሀሳብ ማቅረብ፤ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋማት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተጠሪ ለሆኑ የቁጥጥር ሚና ያላቸው የአስተዳደር ተቋማት፣ ለአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ቢሮዎች እና ተጠሪ የስራ ክፍሎች፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮች፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ለሚዲያ ተቋማት አመራሮች በአዋጁ ዙሪያ ንቅናቄ በመፍጠር እንዲሁም አዋጁን ለማስፈጸም ስለሚኖራቸው ሚና የጋራ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት አዋጁ በተሻለ ሁኔታ እንዲፈጸም ጥረት ማድረግ የእቅዱ አካል ተደርገዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው የመንግሥት የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ የስራ ግምገማ ላይ በአርባ ምንጭ የተደረገው መድረክ በተሳካ መንገድ እንዲዘጋጅ ከፍተኛ ትጋትና ጥረት ላደረጉት የፌደራል ህጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለሆኑት ለወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
በሽልማት አሰጣጡ ወቅት የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ሽልማቱ የተቋሙን ዓላማ ለማሳካት በትጋት የሚሰሩ ሰራተኞችን እውቅና መስጫ አንዱ መንገድ መሆኑንና በቀጣይም በተመሳሳይ መንገድ የተሳካ ስራ ለሚሰሩ ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ወቅቱን ጠብቆ እውቅናና ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው የስራ ክፍሎች ስራዎችን በትጋት፣ በቅልፍናና በጥራት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡