በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር የብሔራዊና ክልላዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረቶች ተቋማዊ አቅም ዳሰሳ (Organizational Capacity Assessment) ግኝት ላይ የብሔራዊና ክልላዊ ትብብር ጥምረቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የአባል ተቋማት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ አያሌው ፍልሰትን በአግባቡ ከማስተዳደር አንፃር መንግሥት በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀው በተለይም የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት እንዲሁም ብሔራዊና ክልላዊ የትብብር አደረጃጀቶችን በመዘርጋት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ አሰግድ እነዚህን የወጡትን ህጎች እና የተዘረጉትን አደረጃጀቶች ወጥ በሆነ መንገድ ከማደራጀት አኳያ ውስንነቶች የነበሩ በመሆኑ በተቋማችን የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር እነዚህን ውስንነቶች ሊፈታ በሚችል መልኩ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመውን ብሔራዊ የትብብር ጥምረቱን ጨምሮ በተመረጡ ስምንት ክልሎች ላይ የብሔራዊና ክልላዊ ትብብር ጥምረቶች ተቋማዊ አቅም ዳሰሳ እንዳደረገ ገልጸዋል፡:
በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ እያሱ ቀለሜ በበኩላቸው የተቋማዊ አቅም ዳሰሳ ጥናቱ በእነዚህ ጥምረቶች የፍልሰት አስተዳደርና አደረጃጀት፣ አጠቃላይ የአስተዳደር ልምዶች፣ ከፖሊስ አውጪዎችና ሌሎች አጋሮች ጋር ያሉ ውጫዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ተቋማዊ መማማሪያነትና ቀጣይነት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ዳሰሳ በማድረግ የተገኙ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ለቀጣይ ስራዎች እንደ ግብዓት በመውሰድ በሰው መነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠርን ጨምሮ ፍልሰትን በአግባቡ ለማስተዳደር የምንሰራበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ጥናቱ የትብብር ጥምረቶችን የመካከለኛና ረጅም ጊዜ አቅምን በመለየትና ቅድሚያ የሚሰጥበትን ሁኔታ በማመቻቸት እንዲሁም የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀትና በቀጣይ ለሚደረጉ ክትትልና ድጋፎች ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አንስተዋል፡:
የብሔራዊና ክልላዊ ትብብር ጥምረቶች ተቋማዊ አቅም ዳሰሳ ሂደት፣ ዓላማ፣ ጠቀሜታ፣ የዳሰሳው ግኝት ዘርዘር ባለ ሁኔታ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አቶ መንግስቱ ታደሰ እና አቶ ታደለ አካሉ እንዲሁም በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ እያሱ ቀለሜ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳብና አስተያየቶች እንዲሁም ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቷል፡፡