በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው ብሔራዊ አስተባበሪ አካል አብይ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግንቦት 6/2018 ዓ.ም አካሂዷል፡፡
በዚህም ወቅት ሴቶች በታሪክ በነበረው ጾታን መሰረት ባደረገ የተዛባ አመለካከት ሕፃናት ደግሞ በአካልና በአእምሮ ያልጎለመሱ በመሆናቸው ምክንያት ለአካላዊ፣ ወሲባዊ ፣ ሥነ ልቦናዊ ፣ኢኮኖሚያዊና እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጥቃቶች/ወንጀሎች ተጋላጭ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወንጀሉ በባህሪው እና በውጤቱ ተጎጂዎች ላይ ከሚያደረስው ጊዜአዊ እና ዘላቂ ዘርፈ ብዙ ጉዳት በተጨማሪ እንደአገር ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ቀውስን የሚያስከትል እንደሆነ ተወስቷል፡፡
ይሁንና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም መንግሥት ወንጀሉን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሕግጋትን የማውጣት፣ የመተግበር፣ ለጥቃቶች መንስዔ የሆኑ አመለካከቶችን፣ ልማዶችን እና እሴቶችን ለመቀየር የሚያስችሉ ስልቶችን መንደፍ እንዲሁም የፍትሕ እና የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች ተደራሽ መሆናቸውን የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት እንደመሆኑ ለድርጊቱ የሚያስፈለገው ምላሽ ሁሉን አቀፍና የተቀናጀ ሊሆን እንደሚገባ በመገንዘብ በተቀናጀና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የህጻናት ፍትሕን ለማረጋገጥ 19 አባላትን የያዘ አስተባባሪ አካል በ2004 ዓ.ም በመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በይፋ ተቋቁሟል።
ይህንንም ተከትሎ አስተባባሪ አካሉ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመሰጠት የሚያስችል ከ2003–2007 ዓ/ም የሚተገበር ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀትና በማጽደቅ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቃተ ሕግ፤ ለወሲባዊ ጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት አገልግሎት የሚሰጡ አንድ ማዕከላት እንዲቋቋሙ እና እንዲስፋፉ የማድረግ፤ በፍርድ ቤት ፣ በዐቃቤ ህግና በፖሊስ ልዩ የችሎትና የምርመራ አደረጃጀቶች የመዘርጋት፤ መጠለያዎችን ማስፋፋት፤ የጤናና የስነልቦና አግልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ፤የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ እና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ለባለሙያዎች ስልጠናዎችን እንዲሰጡ የማድረግ ስራዎችን ጨምሮ በርካታ የመከላከልና ምለሽ የመስጠት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ከዚህ ስትራቴጂ ትግበራ በኋላም ከጥቅምት 2016ዓ.ም እስከ 2020 ዓ.ም የሚተገበር ሁለተኛ ስትራቴጂክ እቅድ በማጽደቅ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፤ ስትራቴጂው ከቀድሞ ስትራቴጂ በተለየ መልኩ በመከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገ እና ምላሽ የመስጠት ፤ መረጃ አያያዝ ስርዓትን የመዘርጋትና ጠንካራ ቅንጅታዊ አስራር መዘርጋት የትኩረት አቅጣጫዎቹ አድርጓል፡፡
እነዚህን የትኩረት አቅጣጫዎችን ለመተግበር በሚያስችለው መልኩ የብሔራዊ አስተባባሪ አካሉን አሰራር ማጠናከርና ትኩረት የሚሹ ተግባራትን በመለየት አገራዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና መተግበር በማስፈለጉ እንዲሁም አባል ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ጥቃትን የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት ስራዎች በተቀናጀ እና ሁሉን አቀፍ በሆነ ስልት እና በእኩል ትኩረት ለመስራት እንዲያስችላቸው የብሄራዊ አስተባባሪ አካሉን አሰራር በመፈተሸ የአሰራር መመሪያ (Working Procedures Manual) አዘጋጅቶ በዛሬው መድረክ በማቅረብ አፀድቋል፡፡
በተያየዘም በመድረኩ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መረጃ አያያዝ ሥራዓት(GBVIMS) እና በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መረጃ ስርዓት (CRIMS) በማስተዋወቅ በሴቶች የአንድ ማዕከላት ጥናት ድርጊት መርሃ-ግብር እንዲሁም የስትራቴጂው አፈፃፀም ግምገማ ላይ በተቋማቱ የበላይ አመራሮች ቀጣይ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡
መድረኩን የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን አዘጋጅተውታል፡፡