በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የ2016 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀሙን የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ እና የዘርፉ መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ገምግሟል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ የግምገማ መድረኩን ሲከፍቱ እንደገለፁት በዘርፉ በ2016 በጀት ዓመት ውስጥ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ፣ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን ለሕግ ከማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ከማድረግ እንዲሁም በሙስና ወንጀል የተመዘበሩ የሕዝብና የመንግሥት ሐብት በማስመለስ የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም ከማስጠበቅ ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ በረከት ማሞ ያቀረቡ ሲሆን የምርመራ መዛግብት ማጥራት አፈፃፀም በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ፣ በሙስና፣ በኢኮኖሚ እና በልዩ ልዩ ወንጀሎች በበጀት ዓመቱ ውስጥ በአጠቃላይ በ55,925 መዝገቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ውሳኔዎችን መስጠት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የሪፖርቱን መቅረብ ተከትሎ በስራ አፈፃፀም ላይ በታዩ ክፍተቶች እና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የመፍትሔ ሃሳቦች እና አቅጣጫዎችም ተሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይ በጀት ዓመት በሙስና የተመዘበሩ ሐብት ከማስመለስ፣ የተደራጁና ደንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ላይ በጥናት የተመሰረተ ምርመራ እና የክስ ስራዎችን በማከናወን፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ተቋማት ጋር ትብብርና ቅንጅትን በማጠናከር ስራዎችን በውጤታማነት መፈፀም እንደሚገባ የስራ አቅጣጫ በማስቀመጥ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡