የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር Hague Institute For Innovation Of Law (HIIL) ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር የማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕን በኢትዮጵያ ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በዛሬዉ እለት ተፈራርሟል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ እና የHIIL ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚና መስራች ዶ/ር ሳሙኤል ሙለር የማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕን በኢትዮጵያ ለማጠናከር በሚሰራዉ ስራ ላይ ስላሉ ምቹ ሁኔታዎች፣ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሀሳቦች ብሎም የትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ፣ የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፎች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዉ ተወያይተዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ በውይይቱ ወቅት HIIL በፍትሕ ሴክተሩም ሆነ ከሌሎች ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት ሰፊ ልምድ ያለዉ በመሆኑ ፍትሕ ሚኒስቴር ከዚህ ድርጅት ጋር አብሮ በመስራቱ ደስተኛ መሆናኑን ገልፀዉ በተለይም የሶስት አመቱ ፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንዱ አምድ በሆነዉ የማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማጠናከር በሚያስችሉ ተግባራት በመሳተፉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዶክተር ሳሙኤል ሙለር በበኩላቸው ድርጅታቸዉ HIIL የፍትሕ ሴክተሩን ለመደገፍ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያደርገዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለጉዳዩ ቅድሚያ እንደሚሰጥም ገልፀዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን ድርጅቱ በተለይም የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎትን ለማጠናከር በሶስት ክልሎች ማለትም በአዲስ አበባ፣ በአፋርና በሲዳማ ለሚከፈቱ ሶስት የመጀመሪያዎቹ ማእከላት የሚዉል ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።
የማኅበረሰብ የፍትሕ አገልግሎትን ለማጠናከር ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ገደማ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸዉን ያስታወሱት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታዉ የሕግ ችግሮች ከሚስተዋሉባቸዉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የመሬት ፍትሕ ጉዳይ መሆኑን አንስተው በዚህ ጉዳይ ላይ የሚታዩ ልዩነቶችን ለመፍታት ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርኣቶች ሚናቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ለዘርፉ ተዋንያን አጋዥ የሆነ ሰነድ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመሆን HIIL ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህንና መሰል የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎት የሚሰጡ ማእከላትን መገንባትና አስፈላጊዉን ግብአትና እገዛ ለማድረግ ድርጅቱ በዛሬዉ ስምምነት ለአንድ ዓመት እና ወደፊትም በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት መፈረሙንና ይህም የሕግ ሥርዓት ዉስጥ አዎንታዊ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ለመጠቀም ያስቻለ ክስተት ተደርጎ እንደሚወሰድ በመግለፅ ሚኒስትር ዴኤታው ድጋፍ ለሚያደርገዉ Hague Institute for Innovation of Law (HIIL) ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ሳሙኤል ሙለር በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የማኅበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት ማአከላት እጅጉን አስፈላጊ መሆናቸዉን በማረጋገጥ በዚህ እና በመሰል ጉዳዮች ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸዉን ስምምነት በመፈራረማቸዉ እጅግ ደስተኛ መሆናቸዉን አክለዋል፤ ወደፊትም አብረዉ በሚሰሩባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ ከክብርት የፍትሕ ሚኒስትሯ ጋር ጥሩ ምክክር ማደረጋቸዉን አመላክተዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን እና በ Hague Institute for Innovation of Law (HIIL) በኩል በዶ/ር ሳሙኤል ሙለር አማካኝነት ተፈርሟል፡፡