"ኢትዮጵያን አለምአቀፍ የግልግል ዳኝነት (Arbitiration) ማእከል ለማድረግ ፍትህ ሚኒስቴር በባለቤትነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነዉ" ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ

"The Ministry of Justice is Working with Ownership and Focus to Make Ethiopia an International Arbitration Center" Honorable Ato Belayhun Yirga

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በባለቤትነት ኢትዮጵያን አማራጭ አለመግባባት (የሙግት) መፍቻ ማእከል ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ገለፁ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ አማራጭ የግልግል መፍቻ ሥርዓትን እንደ አንድ የፍትሕ ስርአቱ አካል አድርጎ በመዉሰድ ኢትዮጵያን ዓለም ዓቀፍ የግልግል መፍቻ ማእከላት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዉ አማራጭ የግልግል መፍቻ ሥርዓት ማለት ከፍርድ ቤት ዉጭ ሌላ አስገዳጅ በሆነ መንገድ አለመግባባት ሚፈታበት ሥርዓት መሆኑንና ይህ ሥርዓት አስገዳጅነቱ ከፍርድ ቤት ጋር የሚያመሳስለዉ ባህሪ ሲሆን ከመደበኛዉ የፍትሕ ሥርዓት የተሻለ ከሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች ዉስጥ ዉሳኔ የሚሰጡ አካላት ባልተግባቡት ሰዎች ማለትም በሁለቱም ተዋዋዮች አማካኝነት የሚመረጡ መሆኑ ነዉ፡፡

ዉሳኔ የሚሰጡ አካላት አስገዳጅ የሆነ ዉሳኔ ሲሰጡ በተቻለ መጠን ሁለቱንም ወገኖች ያቀራረበና ተጠቃሚ የሚያርግ አይነት ዉሳኔ የሚሰጡ መሆኑ ሌላዉ ሲሆን ከፍርድ ቤት አካሄድ በተሻለና ባጠረ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑና በተጨማሪም አለመግባባት የሚፈጠርባቸዉ ጉዳዮች ቴክኒካል ነገሮችን የሚፈልጉ ከመሆናቸዉ ጋር ተያይዞ እነዚህ ዉሳኔ የሚሰጡ አካላት በተዋዋይ ወገኖች የሚመረጡ በመሆናቸዉ በጉዳዩ ላይ የተሻለ ሙያና እዉቀት ያላቸዉ መሆናቸዉ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሰርአትን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

አገራችንም በርካታ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች እያደረገች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያን አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ማእከል ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸዉን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዉ አማራጭ አለመግባባት መፍቻ ማእከላትን አንድ አገር ላይ ለመክፈት ከሚያስችሉ መክንያች አንደኛዉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗን ማረጋገጥ መሆኑንና ለአብነትም የአፍሪካ ህብረት፣የተመድ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗን አንስተዉ በተጨማሪ የምስክርና የማስረጃ ጉዳይ በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ ለማስቻልም አህጉር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አንድ ትልቅ እድል እንደሚወሰድ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር ተያይዞ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ በማብራሪያቸዉ ያነሱት ክቡር አቶ በላይሁን አለምአቀፍ ኢንቨሰተሮች ወደ አንድ አገር ኢንቨስት ለማድረግ ሲመጡ ከሚያስቀምጧቸዉ መስፈርቶች ዉስጥ እንደ አንድ መስፈርት የሚያዩት አለመግባባት ቢፈጠር በአጭር ጊዜ ዉስጥ መፍታት የሚያስችል ሥርዓት መኖሩን ማረጋገጥ ሲሆን ለዚህም አማራጭ አለመግባባት መፍቻ ማእከላትን ለማቋቋም እንደ አገር ፍትሕ ሚኒስቴር በባለቤትነት ኢትዮጵያ አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ማእከል ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡

ሌላዉ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ትኩረት ካደረገባቸዉ አንዱና ዋና ትኩረት የሆነዉ የቢዝነስ አጀማመርን ቀላል ማድረግ ሲሆን ይህንን ሁኔታ ምቹ የሚያደርጉ በርካታ የሕግ ሪፎርሞች የተደረጉ መሆናቸዉን ክቡር ሚኒሰትር ዲኤታዉ ያብራሩ ሲሆን ከነዚህ ሪፎርሞች መካከልም አንዱ ከስልሳ ዓመት በፊት ወጥቶ የነበረዉን የንግድ ሕግ መሻሻሉ፣አማራጭ አለመግባባት መፍቻ ሥርዓት ጉዳያቸዉን መፍታት የሚፈልጉ አካላት ጉዳያቸዉን በቀላሉ መታየት እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ የወጣዉ የግልግልና የእርቅ አሠራር አዋጅ ቁጥር 1237 ሌላኛዉ ሲሆን ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚወሰኑ ዉሳኔዎች በሌሎች አገራት ፍርድ ቤቶች ላይ በቀላሉ እንዲፈፀም የሚያስገድደዉ የኒወርክ ኮንቬንሽን እንዲፀድቅ ተደርጓል ሲሉ በዚህም ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ማእከላት የሚወስኑትን ዉሳኔ በሌላ የአለም አገራት አንዲሁም ሌላ አገራት ላይ የተወሰነ ዉሳኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተፈፃሚ አንዲሆን የሚያስገድድ በመሆኑ እድል ይፈጥራል፡፡

በተያያዘም በቅርቡ የሚፀድቅ የግልግል ማእከላትን የአሠራር ሥርዓትን የያዘ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ሌሎች ትላልቅ የግልግል ማእከላትን ለማቋቋም የሚያስችሉ ረቂቅ ደንቦችም መዘጋጀታቸዉንም አያይዘዉ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያን የዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ማእከል ለማድረግም የሌሎች አገራት አሠራር ልምድ ማየት በማስፈለጉ በቅርቡ ፍትሕ ሚኒስቴር ከአይ አረብ አፍሪካ ጋር በጋራ ያዘጋጁት አለምአቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄዱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዲኤታዉ በዚህ ኮንፈረንስም በርካታ የአገር ዉስጥና የዉጭ አገር ተሳታፊዎችና የተለያዩ የግልግል ዳኝነት ማአከላት መሳታፈቻዉንና ከነዚህም ዉስጥ permanent court of arbirtiration ከኒዘርላንድ እንዲሁም london court of international arbitration እና ሌሎች ማእከላት ጋር ኢትዮጵያ ዉስጥ ማእከላትን እንዲከፍቱ ለማድረግ የጎንዮሽ ዉይይት በማድረግ የማግባባት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አለምአቀፍ አለመግባባት መፍቻ ማእከል እንድትሆን ማድረግ በርካታ ጠቀሜታዎች የሚኖረዉ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዉ ለግልግል ዳኝነት የሚወጡ በርካታ ወጭዎችን የሚቀንስ መሆኑ የመጀመሪያዉና ዋነኛዉ መሆኑንና ፣ኢትዮጵያ ዉስጥ በርካታ አለምአቀፍ ድርጅቶች ኢንቨስትመንት እየጀመሩ ሲሆን ከነዚህ ድርጅቶች ስምምነት ሲያደርጉ አለመግባባት በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳዩ የሚፈታበት አግባብ አንዱ የሚነሳ ጉዳይ ሲሆን ማእከላቱን መክፈት እነዚህን ችግሮች ይፈታል ሲሊ በተጨማሪም ራሱን የቻለ የገቢ ምንጭ ኢንዱስትሪ ከመሆኑም ባሻገር ኢንቨስተሮች ወደ አገራችን እንዲመጡ ያበረታታል ሲሉም አክለዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዉ በመጨረሻም ኢትዮጵያን የዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ማእከል ለማድረግ ከሚያስችሉ ጉዳዮች አንዱ የሆነዉ ኮንፈረንስ ማድረግ የሚያስችል አቅም አላት ወይ? እንዲሁም ወደ አገሪቱ የሚመጡ የግልግል ዳኝነት ማእከላት ባለሙያዎችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም አላት ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ የሚሆንና መሬት ላይ እየተሰራ ያለዉን ስራ ማሳያ የሆነዉ በቅርቡ የተካሄደዉ ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንስ ሲሆን በዚህ ኮንፈረንስ ላይም በኮንፈረንሱ ተሳታፊ የነበሩ ማእከላት አገራችን ላይ የግልግል ዳኝነት ማእከላትን እንዲከፈቱ ለማድረግ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ ሁኔታ ያመላከተችበት ብሎም ልምዷን ያጋራችበት እንደነበር አንስተዋል፡፡

Tagged Under: Arbitration International law Legal Reform
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች