በፌዴራል ጠበቆች እና የጥብቅና ድርጅቶች የስነምግባር ጥሰት፣ ጥቆማ አቀራረብ፣ የምርመራ እና ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም የእድሳት ጊዜው ያለፈ የጥብቅና ፍቃድ ላይ የሚጣል መወሰኛ ረቂቅ መመሪያን አስመልክቶ ጠበቆች በተገኙበት ህዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም የግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሂዷል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር እና የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ረታ ንጋት መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት የፍትሕ ሚኒስቴር ጠበቆችንና የጥብቅና አገልግሎትን የማስተዳደር እና የመቆጣጠር ኃላፊነት እና የስነ-ምግባር ጥሰት ጥቆማ በቀረበ ጊዜ የስነ-ምግባር ጥሰት ስለመፈጸሙ ለማረጋገጥ ምርመራ የማካሔድ እና የዲሲፒሊን ክስ የመመስረት ሥልጣንና ተግባር በሕግ የተሰጠው በመሆኑ ሥልጣንና ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል ረቂቅ መመሪያው መውጣቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ ረታ አያይዘውም የጥብቅና አገልግሎት የዜጎች መሠረታዊ እና ህገ-መንግስታዊ መብቶች ከሆኑት ፍትሕ የማግኘት፣በጠበቃ የመወከል እና ከሌሎች መብቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ እንዲሁም በአጠቃላይ በፍትሕ ስርኣቱ፣በሕዝብና መንግሥት ጥቅም ላይ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ማንኛውም ሰው በጥብቅና አገልግሎት ላይ የስነምግባር ጥሰት ሲፈፀምበት ለፍትሕ ሚኒስቴር ጥቆማ ማቅረብ እንዳለበት አውስተዋል፤ አክለውም የስነምግባር ጥሰት፣የቅሬታ አቀራረብ ፣ የምርመራ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ግልፅና ተጠያቂነትን የተላበሰ መሆን ያለበት በመሆኑ መመሪያዎቹ ላይ ተሳታፊዎቹ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ገንቢ ግብዓት የሚሆን ሀሳብ እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
በመቀጠል ረቂቅ መመሪያዎቹ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የቀረበውን ረቂቅ መመሪያ ተከትሎም ጠበቆች በመመሪያው ላይ መሻሻል፣ መጨመር ፣ መቀነስ እንዲሁም መዳበር አለባቸው ያሉትን እና ቢብራሩ ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም ከተወያዮች የተነሱ ነጥቦችን አስመልክቶ ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ማብራሪያ እና ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን በአብዛኛው ከተሳታፊዎች የተነሱ ሃሳቦች በግብዓትነት እንደሚወሰዱ ተጠቅሷል፡፡
በቀጣይ የኦን ላይን የግብዓት ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚከናወን ከመድረክ ተጠቁሟል፡፡