በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ከፍትሕ ለሁሉም ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ /Justice For All- PF Ethiopia/ ጋር በመተባበር በሕግ ማርቀቅ እና በአዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ላይ ከፌዴራል እና ከተለያዩ ክልሎች ለተወከሉ ከ100 በላይ ዐቃብያነ ሕግ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር በዓመቱ ውስጥ የሚሰጣቸው የሥልጠና ርዕሰ ጉዳዮችን ለመለየት በሚያደርጋቸው የፍላጎት ደሰሳ ጥናት ውቶች መሠረት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ባለሙያው በእውቀትና በክህሎት የዳበረ እንዲሆን የማድረግ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከሕግ ማርቀቅ ጋር በተያያዘ በተለይም ለፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማነት ካለው ሚና አኳያ አንድ ሕግ እንዲረቀቅ ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው እና ወቅቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ የባለሙያዎችን አቅም በሥልጠና በየጊዜው ማሳደግና እንዲሁም የተገኘውን አቅም በተገቢው መንገድ ተጠቅሞ ውጤታማ ሥራን ማከናወን እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ስልጠናው አዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017ን በተመለከተ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ውስብስብ እየሆኑ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ይሄንን የሚመጥን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ከመዘጋጀቱ ጋር ተያይዞ ባለሙያው መመሪያውን በሚገባ ተረድቶ በአዲሱ የሥራ ዘመን ተግባራዊ እንዲያደርገው የጋራ የሆነ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
ከሚሰጠው ሥልጠና ጎን ለጎን መድረኩ ተሳታፊዎች በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ የዕርስ በርስ ልምድ ልውውጥ በማድረግ የሚማማሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡