አገኘሁ ገድይሁን አጋሉ የተባለ ተከሳሽ በ8/10/2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ሲሆን በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ጎሮ አፍሪካ ክሊኒክ በመባል በሚጠራው አከባቢ ከባለቤቴ ጋር አለያይታኛለች በሚል ሟች ብርቱኳን አበራ ወደ ቤትዋ ስትሄድ ዛፍ ስር ተደብቆ ጫፉ ስለት ባለው ፌሮ ብረት የተለያየ የሰውነት አካሉዋ ላይ በመውጋት ሕይወትዋ እንዲያልፍ በማድረጉ ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ህ/አ 539/1/ሀ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ሶስት የመከላከያ ምስክሮች በማቅረብ ያሰማ ቢሆንም የቀረበበትን ክስ ሊከላከል ባለመቻሉ ፍ/ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሽ በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውስኖበታል፡፡