የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ከፌደራልና ከክልል ለተውጣጡ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ም/ሃላፊዎቸ፣ የፍትሕ ቢሮ ምክትል ሃላፊዎች እና ባለሞያዎቸ በህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ የ3 ቀን ሥልጠና ተስጠ።
በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ በሥልጠናው መግቢያ ላይ እንደተናገሩት ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መከላከል እና ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑን በመግለጽ ሥልጠናው ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ሀላፊዎችና ባለሞያዎች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተሞክረው በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ስትራቴጂዎችን (INSPIRE) ሥልጠና በመስጠት እንደ ሀገር በተቀናጀ መልኩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የህጻናትን ፍትሕ ለማረጋገጥ የተዘጋጀው ብሔራዊ ስትራቴጂን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም በሥልጠናው ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምንነት; ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለመቀነስ እና ተፈጽሞ ሲገኝ ደሞ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ያሉ ስትራቴጂዎችና ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታና ከተቀረጸው ስትራቴጂ አንጻር እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ሰልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙን ግንዛቤ በስራቸው ተግባራዊ በማድረግ የህጻናት ደኅንነት እና መብት ለማስጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሥልጠናው በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ እና ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ባካበቱ ባለሞያዎች ለሶስት ተከታታይ ቀናት ተሰጥቷል ።