ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ ለመደበኛው የፍትሕ ስርአት አጋዥ እንዲሆኑ ማስቻል እንደሚገባ ተመላከተ

Traditional Dispute Resolution Mechanisms Should Gain Legal Recognition to Complement the Formal Justice System

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ለማካተት የሚያስችል አገራዊ የምክክር አውደ ጥናት የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሰኔ17/2017 ዓ.ም አካሂዷል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ አገራችን በባህላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት ለረዥም ጊዜ የኖረ ታሪክ ባለቤት መሆኗን አስታውሰው፣ እነዚህ የፍትሕ ስርአቶች ተገቢውን የሕግ እውቅና ሳያገኙ በመቆየታቸው ለመደበኛው ሥርዓት አጋዥ መሆን በሚገባቸው ልክ ሳይሰራባቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

የባህላዊ የግጭት አፈታት ሲተገበርም በትክክለኛውን ሥርዓትና መሠረታዊ መርሆዎችን ተከትሎ መሆን እንደሚገባውና በተለይም በዳይና ተበዳይን ባማከለ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ፣ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትኩረት መስጠትንና የባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት መርህን በተከተለና እሴትን በማይሸረሽር መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ጉዲዮች ሊሆኑ እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን ዶ/ር በበኩላቸው ለረዥም ዘመን ማህበረሰቡን በሰላምና በሥርዓት ያሸጋገሩ የግጭት አፈታት ስርአቶቻችን ከፍተኛ ዋጋ በመገንዘብ የሕግ እውቅና እንዲያገኙ፣እንዲበረታቱ እና የበለጠ እንዲስፋፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፣ ባህልንና ወግን ከማክበር ጎን ለጎን ሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ፣በጥንታዊ ጥበብና በዘመናዊ ህጋዊ መርሆዎች መካከል መናበብና ድልድይ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የወርልድ ቪዥን ሃላፊ ተወካይ አቶ ሳሙኤል ጥላሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአገር በቀል የግጭት አፈታት የፍትሕ ስርአቶችን ለመምራት እያደረገው ላለው አገራዊ አስተዋፅኦ አድናቆታቸውን ገልፀው ድርጅታቸው ፍትሕንና የማኅበረሰብ ሰላምን የሚያጎለብቱ ስራዎችን በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በኢትያጵያ የሕግ ስነ-ሥርዓት ውስጥ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴን ለማካተት መወሰድ የሚገባቸው ወሳኝ እርምጃዎች እንዲሁም የአምስት ክልሎች የማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የመወያያ ሰነድ በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያና የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት እና በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን፤ የባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች መተግበር አስፈላጊነት ውስጥ አንደኛው በአለም ዙሪያ ተደራሽ መሆናቸው አንስተው ይህንኑ ተከትሎ በአገራችን ላሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና በመስጠት ሂደት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን በማንሳትና በመወያየት የፍትሕ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል።

በመድረኩ ለባህላዊ ግጭት መፍቻ ዘዴዎች እውቅና በመስጠት ሂደት ውስጥ በቀጣይ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የምክክሩ ተሳታፊዎችም የቀረቡ የመወያያ ሀሳቦች ግንዛቤ የፈጠረላቸውና ለስራው መሳካት እንዲተጉ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀው በየ ክልሎቻቸው ነባራዊ ሁኔታ እና ባህልና እሴቶች ላይ ተመስርተው ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል።

Tagged Under: access Access to Justice civil liberties conflict customary customary justice dispute formal fundamental rights Human Rights Justice legal legal recognition Legal Reform mechanisms participatory justice recognition resolution Rule of Law system traditional traditional dispute resolution vision world
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች