የኢትዮጵያ የመሬት ፍትህ አመላካች ሰነድ (Guidelines) ተዘጋጅቶ ተመረቀ

Ethiopian Land Justice Guidelines Document Prepared and Inaugurated

ፍትሕ ሚኒስቴር ከሄግ ኢኖቬሽን የሕግ ተቋም ጋር በመተባበር ከመሬት ጋር የተያያዙ ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል ልምድና ተሞክሮን የያዘ የኢትዮጵያ የመሬት ፍትሕ አመላካች ሰነድ ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ በሰነድ ዝግጅቱ የተሳተፋ ባለሙያዎች፣ የሄግ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።

በተያያዘም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው የኦሮሚያ ባህል ፍርድ ቤቶች አዋጅን አስመልክቶ የሕግ አፈፃፀም የተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ሪፓርት ቀርቧል።

ኢትዮጵያ በሶስት አመቱ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ከያዘቻቸው አስር አምዶች ውስጥ የመሠረተ ማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕን እውን ማድረግ አንዱ መሆኑን የገለፁትና ይህንን ለማሳካት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት በቅድሚያ በጥናት መለየት አስፈላጊ በመሆኑ ፍትሕ ሚኒስቴር እና ሄግ ኢኖቬሽን የሕግ ተቋም ባካሄዱት ጥናትና ግኝቶች ተመስርቶ ህብረተሰቡን መሠረት ያደረጉ ጥያቄዎችን ለመፍታት ማህበረሰቡ በእለት ተእለት እንቅስቃሴ ግጭቶች ሲያጋጥሙት ሲፈታባቸው የቆዩ ልምዶችን መደበኛ ወደሆነው የሕግ አግባብ ለማምጣትና በተገቢው መንገድ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።

በዚሁ መሠረት መሬት ለኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫ በመሆኑ ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያ የመሬት ፍትሕ አመላካቸ ሰነድ ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ይፋ መደረጉን በመግለፅ በዚህ ስራ ለተሳተፉ ለሄግ ኢኖቬሽን የሕግ ተቋም ፣ለዴስትኒ ኢትዮጵያ፣ ሌሎች የዘርፉ ኤክሰፐርቶች እና ሰነዱን ላዘጋጁ የኮሚቴ አባላት እንዲሁም ለኦሮሚያ የፍትሕ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

የሄግ ኢኖቬሽን የሕግ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሳሙኤል ሙለር በበኩላቸው አመላካች ሰነዱን ለማዘጋጀት ከጅምሩ ጀምሮ መረጃ በመሰብሰብ፣የዳሰሳ ጥናት በማድረግና በማስረጃ የተደገፈ ሰነድ ለማዘጋጀት በርካታ ሂደቶችን አልፎ በዛሬው እለት ይፋ መደረጉን አንስተው በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የመሬት ፍትሕ አመላካች ሰነድ ገዥ የሆነ ህጋዊ ሰነድ ባይሆንም በመሬት ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት በተለይም ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉና በመሬት ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ተዋንያን ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ሰነድ እንደሆነ እና ለፖሊሲና በዘርፉ ለሚኖረው ፍትሕ አሰጣጥ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ ልምዶችና ተሞክሮዎችን የያዘና ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ሂደቶችን ማካተቱ ተጠቅሷል።

ሰነዱ ሲነደፍም ከባህላዊና መደበኛ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ውስጥ ልምዶችን በመውሰድና በማቀናጀት የኢትየጵያ የመሬት ፍትሕ ለሁሉም ፍትሀዊ፣ዘላቂ እና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ በማለም መሆኑ ተገልፆል። በእለቱም በሰነድ ዝግጅቱ ለተሳተፉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል

በሌላ በኩል ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የኦሮሚያ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ትግበራ የሕግ ተፅእኖ ግምገማ የቀረበ ሲሆን ህብረተሰቡ ከመደበኛው ፍርድ ቤት ይልቅ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ተመራጭ እያደረገ መሆኑንና ለማሳያም በ2016 ዓ.ም 313,520 አዳዲስ መዝገቦች በኦሮሚያ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተከፍቶ ከ294 ሺህ በላይ መዛግብት ከሳሽ እና ተከሳሽን በሚያስታርቅ መልኩ መፍትሄ ማግኘታቸው ተገልፆል። የዚህ የተፅዕኖ ግምገማ ዋነኛ ዓላማ በመሰረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አፈፃፀም በክልሉ የባላዊ ፍርድ ቤቶች የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ለማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም የተገኘውን መልካም ልምድና ተሞክሮ ለማሳፋት እድል የሰጠ ጥናት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

Tagged Under: Conflict Resolution Legal guidelines
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች