በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ የተመራ ልኡክ ቦንጋ ሚዛን አማን ከተማ በመገኘት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ገመገመ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ የተመራ ልኡክ ቦንጋ ሚዛን አማን ከተማ በመገኘት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ገመገመ • A high-level delegation led by H.E. Mrs. Hanna Arayaselassie, Minister of Justice of the FDRE, visited Bonga Mizan Aman City to evaluate the implementation of the Justice Transformation Plan.

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ የተመራ እና የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃንን ያካተተ የአገራዊ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የድጋፍና ክትትል ቡድን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የሁለት ዓመት የትራንስፎርሜሽን አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ቦንጋ እና ሚዛን አማን ከተማ ተገኝተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ወደ ክልሉ ሲገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ክቡር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ እና የክልሉ የፍትሕ ዘርፍ አመራሮች አቀባበል ያደረጉላቸዉ ሲሆን በመቀጠል የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በክልሉ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመታት አፈጻፀም ሐምሌ 02 እና 03 ቀን 2017 ዓ/ም በጥልቀት ገምግሟል።

ክብርት የፍትሕ ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ ክልሉ ላደረገው አቀባበል አመስግነው የመድረኩ ዓላማ በአገር ደረጃ የታቀደው የሶስት ዓመት የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ የደረሰበትን ደረጃ ለማየትና አስፈላጊውን ቅንጅትና ትብብር ለማድረግ ብሎም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን በበኩላቸው የፍትሕ ሚኒስቴር አገር ዓቀፍ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለመተግበር ከክልሎች ጋር በትብብርና በቅንጅት እንደሚሰራ እና ተከታታይነት ባለው መልኩ የክልሎችን አፈፃፀም በመገምገም ጠንካራ ድጋፍና ክትትል የማድረግ አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡ በመቀጠልም የክልሉ የሁለት ዓመታት የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ ከትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አስር አምዶች አኳያ የተከናወኑ ተግባራት በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በተለይም በማኅበረሰብ ዓቀፍ ፍትሕ አገልግሎት አምድ ስር ክልሉ የባህላዊ ዳኝነት አዋጅ አውጥቶ በመተግበር ላይ መሆኑ፣ የአስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጅ በክልሉ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውዝፍ መዝገቦች የማጥራት ስራዎች መከናወናቸው፣ የተቋረጡ መዝገቦችን መልሶ ለማንቀሳቀስ ሥራዎች መሠራታቸው፣ የይቅርታ አሰጣጥ መመሪያ መሻሻሉ፣ የሚጣሉ የገንዘብ ቅጣቶች ገቢ ለማድረግ ሥራዎች መሰራታቸው ተገልጿል፡፡

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ አምድ ስርም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ መሆኑ፣ የንቃተ ሕግ በክልሉ በሚገኙ ሚድያዎች እየተሰጠ መሆኑና ነፃ የሕግ ድጋፍ በዐቃቤያን ሕግና በዩኒቨርስቲዎች አማካኝነት እየተሰጠ መሆኑ፣ የተከላካይ ጠበቃ ጽ/ቤት ለማደራጀት ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ፣ የፍትሕ አካላት ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም የኅብረተሰብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ክብርት ሚኒስትር ክልሉ የተሻለ እና ጠንካራ አፈፃፀም ማስመዝገቡን አንስተው በማኅበረሰብ ፍትሕ አምድ ስር የተከናወኑ ሥራዎች ለሌሎች ክልሎች አርዓያ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና በአተገባበሩም ወቅት ሰብዓዊ መብትን የተከተለ መሆኑን፣ የሴቶችና ሕፃናትን መብት የሚያከብር መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ፣ የተጀመረው የቅንጅት አሠራርም በፌዴራል ካለው ተሞክሮ በመውሰድ ሥርዓት ተበጅቶለት እንዲመራ፣ በቀሪ ጊዜ ውስጥ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን በትኩረት ለመፈፀም ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ በመጠቆም የፍትሕ ሚኒስቴርም የተቻለውን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በክልሉ የተሰሩ የልማት ሥራዎችን፣ ተግባራዊ የተደረገውን የማኅበረሰብ ፍትሕ ባህላዊ ዳኝነት በሽሽንዳ ወረዳ የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ምልከታ የተደረገ ሲሆን በመቀጠልም የክልሉ ማረሚያ ቤት እና የፍትሕ ቢሮ በመገኘት የመስክ ጉብኝት እና የአረንጓዴ አሻራም የችግኝ ተከላ ተከናውኗል፡፡

በመጨረሻም የተጀመረውን የክልሉን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ለመደገፍ በፍትሕ ሚኒስቴር ደረጃ የተዘጋጁ የታክስና ጉምሩክ ወንጀሎች እንዲሁም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምርመራ፣ ክስ እና የችሎት ማስገንዘቢያ መጽሐፍት (Handbook) ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ አስረክበዋል።

Tagged Under: african charter on the rights and welfare of the child and healthcare administration and control authority arayaselassie arra (agency for refugees and returnees affairs) city Convention on the Rights of the Child convention on the rights of the child (crc) delegation formation handbook high high-level Implementation Justice Justice Sector Transformation Plan justice transformation justice transformation plan level minister minister of justice mizan plan second growth and transformation plan site three-year justice sector transformation plan transformation transformation plan transformation plan implementation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች