ለዐቃብያነ ህግ ሲሰጥ የቆየው የቅድመ ስራ ስልጠና የማጠቃለያ መርኃ-ግብር ተካሄደ

The Conclusion of the Preliminary Training for Judicial Officers on the Administration of Justice

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በ2014 ዓ.ም አዲስ ለተቀጠሩ 18 ዐቃቤያነ ሕግ ለ8 ወራት የቅድመ ስራ ሥልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም የሥልጠናው ማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርኃ-ግብሩ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፍቃዱ ጸጋ፣ የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ እንዲሁም በሥልጠናው መርሃ ግብር በአሰልጣኝነት የተሳተፉ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ሲሆኑ ሥልጠናው ጥራት ባላቸው አሰልጣኞች ሲሰጥ መቆየቱን እና ሰልጣኞችም በሥልጠና ወቅት በጎ ስነ-ምግባርና ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ አክለውም ካሪኩለሙን ለቀረጹ እና ፕሮግራሙን ላስተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተለይም የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ፕሮግራሙን ከማስጀመር ጀምሮ ለነበራቸው የላቀ አስተዋጾ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የቅድመ ስራ ሥልጠናው ሂደት እና አፈፃፀም አስመልክቶ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የሥልጠና ፕሮግራሙን መነሻና ዓላማ ብቁና በአግባቡ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሆነ፣ የሥልጠናው ሂደት እና አፈፃፀም ጥሩ እና በርካታ ጠንካራ ጎኖች የታዩበትና ጥሩ ልምድ የተወሰደበት እንደሆነ እንዲሁም በቀጣይ ለሚሰጠው ተመሳሳይ ሥልጠና በሥልጠናው ሂደት የታዩትን ክፍተቶች መቅረፍና ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በመድረኩ ላይ የሰልጣኞች ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት ሥልጠናው አቅም ባላቸው አሰልጣኞች መሰጠቱን፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና በመስጠት እና ክትትልና ድጋፍ በመስጠት ለነበራቸው ትልቅ ሚና ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው ብለዋል፡፡

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ በሥልጠናው ላይ በአሰልጣኝነት ለተሳተፉ እና ሥልጠናውን ሲከታተሉ ለነበሩ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት አሰጣጥ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን ሰልጣኞቹ ዐቃቤያነ ሕግ ስራቸውን ሲጀምሩ የሚገቡት የቃለ-መሀላ ስነ-ስርዓትም በፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃብያነ ሕግ አስተዳደር ጉባኤ ሰብሳቢ በሆኑት በአቶ ገብሩ ገበየሁ አማካይነት እንዲፈፅሙ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ለሰልጣኞቹ ዐቃቤያነ ሕግ የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን ፍትሕ ሚኒስቴር በስነ-ምግባርና በላቀ ፈጻሚነት አቅማቸው የተሻለ እና የተሻለ ትምህርት ደረጃ ያላቸውን ሰዎች በጥንቃቄ መልምሎ ወደ ስራ ማስገባት የፍትሕ ዘርፉን ስራ ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን፤ ሰልጣኞችም የወሰዱትን ሥልጠና ከተማሩት ትምህርት ጋር በማቀናጀት ስራ ላይ እንዲያውሉና ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲፈጽሙ አደራ ብለዋል፡፡ከስነ-ምግባር ጋር በተያያዘም በዘርፉ ስትሰማሩ ስራችሁን በታማኝነትና በቅንነት በመሥራት ከሙስና፣ ከጉቦ እና ካልተገቡ አሰራሮች ራቻችሁን ጠብቃችሁ በንጽህና ሀገራችሁ የጣለችባችሁን ኃላፊነት ልትወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አያይዘውም ወደ ተቋሙ ሲቀላቀሉ ከነሱ በፊት ከተቀጠሩና ልምድ ካላቸው ዐቃብያነ ሕግ ልምዶችን ለመውሰድና የተሻለ ስራ ለመሥራት እንዲሁም ልምድ በመውሰድ ካላችሁ እውቀት ላይ ሌላ ዕውቀት ለመጨመር ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Tagged Under: Anti-Corruption • Capacity Building • curriculum development • development • ethics • federal • federal justice and law institute • institute • integrity • judicial • judicial officers • Justice • justice administration • law • legal • Legal Training • oath of office • officers • pre-service • pre-service training • professional • professional development • program • Prosecutors • Training • training program
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች