ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተሰራ ያለው የሰነድ ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው

Technology-Driven Document Authentication and Registration Work Plays a Significant Role in Realizing Digital Ethiopia

ሐረር፤ ግንቦት 28/2016 (ኢዜአ)፡- የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየሰራ ያለው የሰነድ ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ገለጹ።

ሀገር አቀፍ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት 2ኛው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ፣ ኮለኔል የኑስ ሙሉ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ኪኒሶ እንዲሁም የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ ሥራ “ሰዎችን ህጋዊ ካልሆነ የመንደር ውል የሚታደግ ነው”።

ተረጋግጠው የተመዘገቡ ሰነዶችን በማስረጃነት ሲፈለጉ በመስጠት ለፍትሕ ስርዓቱ አጋዥ በመሆን ለሕግ የበላይነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን በማሳለጥ ረገድ የማይናቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም እንዲሁ።

በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተሰራ የሚገኘው የዘርፉ ተግባር ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተያዘውን የመንግሥት ፖሊሲ ከግብ ለማድረስ አጋዥ መሆኑን አቶ በላይሁን አመልክተዋል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን ተገማች፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራቱን የጠበቀና ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እየታገዘ በርካታ የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘና ወጥ የሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ አሠራርና አንድ አገራዊ የመረጃ ቋት እንዲኖር ለማድረግ በሐረሪ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች ተግባራዊ የተደረጉትን አሰራሮች በሌሎች ክልሎች ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ለሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ አሠራር ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆነ የመጣውን ሐሰተኛ ማንነትና ሰነድን ለመከላከልም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው ሥራውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ኪኒሶ በበኩላቸው አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 11 ወራት ከ806 ሺህ በላይ ጉዳዮችንና ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተገልጋዮችን ያለ ቀጠሮ ማስተናገዱን ገልጸዋል።

ተቋሙ ባሉት 15 ቅርንጫፎች በሰጠው አገልግሎት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱና በዚህም የዕቅዱን 143 ነጥብ 9 በመቶ ማሳካቱን አስታውቀዋል።

ማጭበርበርና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመከላከል ረገድ ለተቋሙ ከቀረቡት መካከል 1ሺህ 298 ሐሰተኛ ሰነዶች ተይዘው አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ከማድረግ ባሻገር፣ በርካቶች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የዘመነ የሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ አገልግሎት በማከናወን ዲጅታል -ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደሚሰራም እስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በበኩላቸው በክልሉ የሚገኘው የተቋሙ ቅርንጫፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለተገልጋዮች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው በዚሁ ምክክር መድረክ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

Tagged Under: authentication beliyhun yirga correctional digital Digital Ethiopia digital transformation document Document Authentication document registration federal federal correctional service commission Fraud Prevention government policy harar information Information technology Justice Justice Ministry ministry registration service delivery improvement Services Stakeholder Consultation Technology
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች