በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ በሆኑት አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራና በዘርፉ ስር ያሉ የስራ ክፍሎችን ያካተተ ቡድን በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በመገኘት የቴክኖሎጅ አጠቃቀምን ተቋማዊ ባህል ለማድረግ የሚያስችል የስራ ጉብኝት በዛሬዉ እለት አካሂዷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ጉብኝቱ በዋናነት ዓላማ ያደረገዉ ስራን በአካል ተገናኝቶ ከመሥራት በዘለለ በቴክኖሎጅ በመታገዝ ቀልጣፋ የስራ ስምሪት ለመስጠትና ጊዜን ቆጣቢ የሆነ የአሠራር ሥርዓትን መዘርጋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ልምድ መዉሰድ መሆኑን ገልጸዉ በእያንዳንዱ የስራ ክፍል አመራሩና ሠራተኛዉ የሚገናኝበት ቴክኖሎጅን መሠረት ያደረገ አሠራር ተግባራዊ በማድረግ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አዉስተዋል፡፡
አያይዘዉም በ2016 የበጀት ዓመት እንደ ዘርፍም ሆነ በተቋም ደረጃ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትኩረት ካደረገባቸዉ ተግባራት መካከል አንዱ የአሠራር ሥርዓትን ማዘመን መሆኑንና ለዚህ ተግባርም የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በቴክኖሎጅዉ ዘርፍ የተሻሉ ባለሙያዎችን ያሰባሰበ ፅ/ቤት በመሆኑ እንደ አንድ አጋዥ ለማድረግ የመጀመሪያ ዙር የሆነ ጉብኝት በዛሬዉ እለት መደረጉንና ይህንን ተግባር በመደበኛነት አጠናክሮ ለማስቀጠልም የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በመፈራረም የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህን የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር በመዉሰድ ተቋማዊ ባህል ማድረግ ለማስቻልም በቀጣይ ሌሎች ዘርፎች በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ተገኝተዉ ልምድ እንደሚወስዱ የተናገሩት አቶ በላይሁን ይህ ከሆነ በኋላ የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች በጋራ እየሰሩ ለተቋሙ የሚጠቅም ስራ ይከናወናልም ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር ዲኤታዉ እንደ ተቋምም ሆነ በዘርፍ ደረጃ እስካሁን የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸዉንና በቀጣይ ይህንኑ ተግባር በማጠናከር በቀን ተቀን ስራዎች ተግባራዊ የሚደረጉበት የአሠራር ስርአቶች የሚዘረጉ ይሆናልም ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ምክትል ስራ አስፈፃሚ እና ፕሮግራም ማናጀር የሆኑት ራሄል ይትባረክ በበኩላቸዉ የተቋሙን የቴክኖሎጅ አጠቃቀም አስመልክተዉ ማብራሪያ ሲሰጡ ለአንድ ስራ ዉጤታማነት የሰዉ ኃይል እና የስራዉ አጠቃላይ ሂደት እንዲሁም የምንጠቀማቸው የቴክኖሎጅ መሳሪያዎች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸዉ ተናግረዉ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የሚከተለዉ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ለስራቸዉ ዉጤታማነት ከፍ ያለ ድርሻ እንዳበረከተላቸዉ ተናግረዋል፡፡
ቀጥሎ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አቤኔዘር ፈለቀ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት እየተጠቀመባቸዉ ስላሉ የቴክኖሎጅዎች ዉጤቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለሉኡኩ አቅርበዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉ የልኡኩ አባላትም ለተደረገላቸዉ አቀባበልና ማብራሪያ ምስጋናቸዉን አቅርበዉ የቴክኖሎጅ አጠቃቀምን በተመለከተ ከፍትሕ ሚኒስቴር የስራ ሁኔታ አንፃር ያላቸዉን ጥያቄዎች አንስተዉ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል
በመጨረሻም የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የስራ ሀላፊዎች ወደ ፊት በማንኛዉም ስራ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክት ፅ/ቤቱ ዲጅታል መታወቂያ አዋጅ 1284/2015 ከጸደቀ በኋላ ስራዉን በይፋ እየሰራና ነዋሪዎችን በተለያ ባንኮችና የገቢዎች ፅ/ቤቶች በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡