የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ዉሳኔ ያገኙ የወንጀል መዛግብት ላይ ቅሬታና አቤቱታ ያላቸዉ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነዉ ማቅረብ የሚያስችላቸዉን ኦንላይን ሲስተም ከኢኖቬሽን ሚኒስቴርና ፔራጎ ከተባለ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጁትን ዌብሳይት ስራ አስጀመረ፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና የሪፎርም ስራዎች ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን ሲስተሙን አስመልክተዉ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በፍትሕ ሚኒስቴር የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉን አንስተዉ ከነዚህም ዉስጥ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል መዛግብት ዉሳኔዎች ላይ ተገልጋዮች የሚኖራቸዉን ቅሬታና አቤቱታ ባሉበት ሆነዉ በአነስተኛ ወጭና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ሳይንገላቱ እንዲያቀርቡ ታስቦ ዌብሳይቱ መበልጸጉን ተናግረዋል።
የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መንገድ ቀላልና ቀልጣፋ ሊሆን እንደሚገባ የገለፁት ዶክተር ኤርሚያስ አገልግሎቱ ለተገልጋይ ዜጎች፣ለዘርፉ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ስራቸዉን በብዙ መልኩ እንደሚያግዝ በመግለፅ በተለይም የፍትሕ ስርአቱን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማደራጀት በኩል የራሱ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚኖረዉና በቀጣይም የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩን በዚሁ መልኩ ለማደራጀት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዉ በዚህ ስራ ለተሳተፉ አካላትም ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡
አገልግሎቱ በልደታ የሚገኙ የወንጀል ጉዳይ ዳይሬክቶሬቶች፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ 10 ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች፣ እንዲሁም በድሬድዋና በሀዋሳ የሚገኙትን ፅ/ቤቶችን እንደሚያካትት የቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ጉዳይ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም ማንኛዉም ቅሬታና አቤቱታ ያላቸዉ ተገልጋዮች በ https://www.eservices.gov.et ብለዉ በመግባት ባሉበት ቦታ ሆነዉ አገልግሎቱን ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እናሳዉቃለን፡፡