ኢትዮጵያና የማላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በፍልሰት አስተዳደር፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት በፍትሕ ሚኒስቴር ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጌጎ ተስፋዬ እና የማላዊ ሪፐብሊክ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ክቡር ፒተር ሙኪቶ (Hon. Peter Mukhito) ተፈራርመውታል።
ይህ ስምምነት እንዲጀመርና የድርድር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የተደረገው በብሔራዊ ትብብር ጥምረቱ አማካኝነት ሲሆን፣ ሁለቱ ሀገራት ለዘመናት የቆየውን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በፍልሰት አስተዳደርና በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን የመከላከል እንዲሁም ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራዎችን በጋራ ያከናውናሉ።
ማላዊ «የደቡብ የፍልሰት መስመር» በመባል በሚታወቀውና ከኢትዮጵያ የሚወጡ ፍልሰተኞች መተላለፊያ ሀገር በመሆኗ፣ የፍልሰተኞች ሰብዓዊ መብትና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግና ህገ-ወጥ ዝውውርን ለመግታት የዚህ የሁለትዮሽ ስምምነት ሚና እጅጉን የጎላ ነው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ይህ ስምምነት ለሌሎች ሀገራትም አርአያ የሚሆን ልምድ የሚቀስምበት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ በቀጣይም ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየር የጋራ ኮሚቴዎችን ከማቋቋም ጀምሮ መደበኛ የሆኑ የሕግ ስምምነቶችን የመፈራረም ስራዎች እንደሚከናወኑ ተጠቅሷል።