የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋሙንና በስሩ ያሉ የተጠሪ ተቋማቱን የ2015 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱንና የቀጣይ ሶስት አመታት ስትራቴጅካዊ እቅዱን ለፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ለስታስቲክስ አገልግሎት በማቅረብ ግምገማ ተካሂዶበታል፡፡
በግምገማዉ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን ጨምሮ የተቋሙ ሚኒስቴር ዲኤታዎች፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፣ የስታስቲክስ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮች እንዲሁም ምክትሎቻቸዉና የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የሴክተሮች ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ አልማዝና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የ2015 ዓ.ም ሪፖርትንና እቅዱን ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የስትራቴጅክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደሳለኝ መንግስቴ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት በተሰጠዉ አቅጣጫ መሠረት ሪፖርቱ መዘጋጀቱን ገልፀዉ የፍትሕ ሴክተሩ የራሱ የሆነ የትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ከጠቆሙ በኋላ ይህ ሰነድም ከአዲሱ የሶስት ዓመት የልማት እቅድ ጋር ተናቦ የሚሄድ መሆኑንና የትራንስፎርሜሽን አምዶች ዙሪያም ከክልል የፍትሕ አካላት፣ ከፍትሕ ቢሮዎች እንዲሁም በፍትሕ ሚኒስቴር ዉስጥ ካሉ አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዶበትና የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደስራ ገብቷል ብለዋል፡፡
አያይዘዉም ይህ የሪፎርም ስራ በትኩረት እንዲተገበር በሚኒስቴር ዲኤታ የሚመራ አዲስ አደረጃጀት መፈጠሩንና ይህንን ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠልም በትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ የተካተቱ ነጥቦችን በእቅዱ በማካተት እየተሰራበት እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
በመሆኑም የማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት ስራዎችን የሚመለከቱ ሰነዶች፣ የፍትሕ ዘርፉን አመራሮችና ባለሙያዎች የማጥራት ስራዎች፣ በፍትሕ ሴክተሩ ያሉ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም የተጣጣሙ ባለመሆናቸዉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎች የማሳደግ ስራ ትኩረት ተደርጎባቸዉ እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት አቶ ደሳለኝ የወንጀልና የፍትሕ አስተዳደሩን ለማዘመንና በአዲስ አስተሳሰብ ለመምራት እንዲያስችልም የአጭር፣የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ሰነዶችን በማዘጋጀት እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በቀረበዉ ሪፖርትና እቅድ ላይ በርካታ ሀሳብ አስተያየት እንዲሁም ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸዉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የተሰጡ አስተያየቶች በግብአትነት እንደሚወስዷቸዉ ገልፀዉ ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ከክልሎች ጋር ያለዉ ግንኙነትን በሚመለከት ለቀረበዉ ጥያቄ ግንኙነቱን ለማሻሻል ጥረት መደረጉንና በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት በቅርበት ለመገናኘትና እቅድና ሪፖርታቸዉን ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የክልሎችን እቅድና ሪፖርት በማካተት የተከለሰዉን ሪፖርት በአጭር ጊዜ እንደሚላክም ገልፀዋል፡፡
በተያያዘም ሌላዉና እየቸገረ ያለዉን ጉዳይ ሲያነሱም በተለይም በጎንዮሽ ካለዉ የፍርድ ቤት ቅንጅታዊ አሠራር ከመዘርጋት ጋር በተያያዘ መሻሻሎች እንዳሉና በሚጠበቀዉ ደረጃ ለመጓዝ ግን አሁንም ማነቆዎች እንዳሉ ሚኒስትሩ የገለፁ ሲሆን እንደ አማራጭም ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ጋር የሚገናኙበትን የራሳቸዉ የሆነ መንገድ እንዲፈጥሩ ሀሳብ መስጠት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸዉ ጥሩ ዉይይት መደረጉን አንስተዉ የተነሱ ነጥቦች ዙሪያም መወሰድ ያለባቸዉ ሀሳቦች ተወስደዉ ማብራሪያ በሚፈልጉ ጥያቄዎች ከሚኒስትሩ የተሰጡ ማብራሪያዎች መልካም መሆናቸዉን ከተናገሩ በኋላ በተለይ ዘርፉ በሪፎርም ሂደት ዉስጥ ያለ እንደመሆኑ የእቅድ ስራዉን የተሻለ ከማድረግና ሙሉ የዘርፍ እይታ ከመያዝ አኳያ ከትላንትና ዛሬ መሻሻሎች መኖሩንና ይህንኑ በተገቢዉ መንገድ አስቀጥሎ የተሻለ ለማድረግ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም የዐቃቤ ሕግ ዘርፉ ስራዎች እንዳሉ ሆነዉ ሪፎርሙን የሚመለከቱ ስራዎችን በተለይም ወደ ታች በማዉረድ ከክልሎች ጋር በቅንጅት የመስራቱ ነገር ሊጠናከር እንደሚገባ ገልፀዉ የተቋቋመዉ የቴክኒክ ኮሚቴ የተነሱ አስተያየቶችን በግብአትነት በመዉሰድ ሰነዱን የማዳበር ስራ ሰርቶ ለበላይ አካል እንደሚያቀርብ ገልፀዋል፡፡