የፍትሕ ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ከሌሎች አጋር አካት ጋር በመተባር የተዘጋጀውን በሕግ አወጣጥ ሂደት ዉስጥ የሕዝብና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚመራበትን ማንዋልና የኦንላይን ምክክር ፖርታል አሰመልክቶ ለሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር የትዉዉቅና ይፋ ማድረጊያ መድረክ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡
በሕግ ማርቀቅ ሂደት ዉስጥ የሕዝብና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማረጋገጥ ለሕግ ጥራት ያለዉ አስተዋፅኦ አጅግ ከፍተኛ በመሆኑና ይህንኑ ተግባር ለማጠናከር ተቋሙ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ማንዋልና የኦንላይን ምክክር ፖርታል አዘጋጅቷል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ የተጣለበትን የህጎችን ጥራት የማረጋገጥ ኃላፊነት ለመወጣት ከሚያስችሉት መንገዶች አንዱ በሕግ ማውጣት ሂደት ውስጥ የሕዝብና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መኖርና አስፈላጊ ግብአቶችን ያካተተ ሕግ መውጣቱን መከታተል መሆኑን በመድረኩ የተገኙት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ገልፀዋል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም የሚወጡ ህጎች ላይ በቂ የሕዝብ ተሳትፎ መደረጉን የሚፈተሽበት አሠራር የነበረው ቢሆንም ይህንን የሚቃኝና ለሁሉም ረቂቆች ተግባራዊ የሚደረግ የአሠራር ሥርዓት ያልተዘረጋ መሆኑ ለሚወጡ ህጎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑ በጥናት መለየት መቻሉንም ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል። በመሆኑም ተቋሙ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ሲሰራ ቆይቶ በሚወጡ ህጎች ላይ የሕዝብና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ሥርዓት የሚያመላክት ማንዋልን አዘጋጅቶ ለህትመት አብቅቷል።
ማንዋሉ በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝብን ተሳትፎን በተመለከተ ዝርዝር ሂደቶችን የያዘ ሲሆን የሕዝብ ተሳትፎ ቅድመ ዝግጅት ሂደት፣የተሳትፎ ማረጋገጫ ስልቶች፣ግብአቶች የሚስተናገዱበት ሥርዓትንና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዬችን አንዲሁም የኢ-ኮንሰልቴሽን ስልትን ሌሎች አካቷል።
የኢ-ኮንሰልቴሽን ፓርታል ቀድሞ የነበረውን የምክክር ሥርዓት በተሻለ እንዲከናወን የሚረዳና በአካል በሚደረግ ውይይት የሚፈጀውን ጊዜ፣ሀብትና የሰው ሃይል የሚቀንስ ከመሆኑም በተጨማሪ ከተደራሽነት አንፃርም የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆነ ማኅበረሰብ ጊዜ እና ቦታ ሳይገድበው የሚወጡ ህጎች ላይ ካሉበት ሆነው ሀሳባቸውን የሚገልፁበት በመሆኑ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ የሚያበረታታ መሆኑን ክቡር አቶ በላይሁን ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም በመድረኩ የተገኙ ተሳታዎችን በሕግ ማውጣት ሂደት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድርሻ እና ኃላፊነት ያለንና ያላችሁ በመሆኑ የዚህን ማንዋልና ድረገፅ አስፈላጊነት በመገንዘብ በየተቋማችሁ መተግበር የሚያስችላቸውን አሠራር በመዘርጋት የበኩላቸውን እንዲወጡ አደራ ካሉ በኋላ ድረ ገፁን በማበልፀግ ያገዘውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ለስራው ድጋፍ ያደረጉትን የአውሮፓ ህብረት፣ጂአይዜድ እና የቤክ ፕሮጀክትን አመስግነዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር የሽሩን አለማየሁ በበኩላቸው ይህ መድረክ ሥልጣን የተሰጣቸው ህጋዊ አካላት ደንቦችን፣ መመሪያዎችን እና ህጎችን ሲያወጡ የሕዝብ ወይም የተመረጡ የቡድን አስተያየቶችን እንዲሰበስቡ የሚስችል መሆኑን ጠቅሰው አሰራሩ ተቋማት ለህጋዊ ሰነድ ዝግጅቶች ዜጎችን ያማከለ አካሄድ እንዲከተሉና እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አክለውም ስርዓቱ ዜጎች በሚወጡ ህጎችና ደንቦች ሃሳባችን አልተደመጠም በሚል የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ለመቅረፍ የሚያስችል ሲሆን፤ ይህንን ስርዓት በመጠቀም ዲሞክራሲያችንን ለማጠናከር እና ግልፅነትን ለማጎልበት የሚወጡ ህጎች እነሱን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አስተላፈዋል።
ቀጥሎም የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶክተር የሹሩን አለማየሁ አማካኝነት በጉዳዩ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
መድረኩ የክልል ፍትሕ ቢሮ ሀላፊዎች፣ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተዉጣጡ የበላይ አመራሮች፣የሕግ ክፍል ሀላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።