የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን ጨምሮ ከፌዴራል ሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲቲዩት፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት፣ ከሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን እና ከፌዴራል ግብር ይግባኝ ኮሚሽን የመጡ የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነበር የሩብ ዓመቱ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ የተካሄደው፡፡
የሪፖርት ግምገማ መድረኩን የመሩት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በመግብያቸው ላይ እንዳስታወሱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ፍትሕ ሚኒስቴርም ሆነ ተጠሪ ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን በግልጽ መረዳት እንዲችሉ በተናጠል ከምናከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎን አንድ ወጥ እና ሁሉንም መረጃ የያዘ የዕቅድ እና የሪፖርት ጥንቅር ማዘጋቱ በተሻለ መመራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በአፈጻጸም ሪፖርቱ ውስጥ መካተት ሲገባቸው ያልተካተቱ ተግባራትን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ማድረግ እና በቀጣይ የየተቋማቱን የትኩረት አቅጣጫዎች እና ዋና ዋና ዕቅዶች ላይ በሰፊው መክሮ የተሻለ የትብብር አውድ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
የሚኒስትሩን የመግቢያ መልዕክት ተከትሎ የተጠሪ ተቋማትን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ጥንቅር ያቀረቡት የሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማካሪው አቶ ያሬድ አዲሱ የየተቋሙን የስራ አፈጻጸም ካቀረቡ በኋላ በቀጣይ እያንዳንዱ ተቋም የሚያዘጋጃቸው ሪፖርቶች የተሟሉ እና ሁሉንም ተግባራት ያካተቱ መሆን ያለባቸው ሲሆን ፣የ5 ዓመት እና የ10 ዓመት ፍትሕ ስርዓት ዘርፉ ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት ያደረገ ሪፖርት መቅረብ ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ያሬድ በገለጻቸው የቁልፍ ተግባር አፈጻጸም፣ የዋና ዋና ግንባታ ስራዎች አፈጻጸም፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና የኦዲት አፈጻጻምን የሚመለከቱ ተግባራት በሪፖርቱ ውስጥ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተው በትግበራ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ፣ አጠቃላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ ለሌሎች ልምድ ሊሆኑ የሚችሉ መልካም ተሞክሮዎችን ገላጭ በሆነ መልኩ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረበው የሪፖርቶች ጥንቅር ላይ ሃሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በአስተያየታቸውም እንደ ተቋም የነበራቸውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ፣ ምርጥ ተሞክሮ እንዲሁም ለስራቸው እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ አያይዘውም በቀሩት የበጀት ዓመቱ ወራትም በትኩረት ስለሚከውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተቋማቱን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ጥንቅር እና በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦችን እንዲሁም ከመድረክ የተሰጡ የስራ አቅጣጫዎችን የሚመለከቱ ዘርዘር ያሉ ዘገባዎችን ይዞ እንደሚቀርብ ቃል ይገባል፡፡