የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ (GIZ) ኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር የአስተዳዳር ስነ-ሥርዓት ሕግ አፈፃፀም እና የሰብዓዊ መብት ክትትል እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ምዕራፍን ለማስተባባር የሚያግዙ የተለያዩ ቁሳቁሶችን አበርክቷል፡፡
በጂ አይ ዜድ (GIZ) ኢትዮጵያ በኩል ድጋፉን ያበረከቱት በኢትዮጲያ የመልካም አስተዳዳር ግንባታ ፕሮግራም ማናጀር ዶ/ር ዎልፍ ክርስቲያን ፒተርስ ሲሆኑ ፍትሕ ሚኒስቴርን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ናቸው፡፡
በርክክቡም የፌደራል አስተዳዳር ስነ-ስርዓት አዋጅ ማብራራያ ሰነድ፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እና የፖሊሲው ማስተግበሪያ የታተሙ ሰነዶችን እንዲሁም የአስተዳዳር ስነ-ስርዓት አዋጁን አፈፃፀም ክትትል እና የሰብዓዊ መብት ክትትልን ለማገዝ የሚረዱ ላፕቶፕ ኮምፕዩተሮች እና ታብሌቶች መበርከታቸው ተመላክቷል፡፡
በርክክቡ ወቅት ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ባስተላለፉት መልዕክት ጂ አይ ዜድ (GIZ) ኢትዮጵያ በተለያዩ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ዙሪያ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር አብሮ በመሥራት ላበረከተው ሚና አመስግነው የአስተዳዳር ስነ-ሥርዓት ሕግ ማብራሪያ ሰነድ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ መታተሙ በሀገሪቷ የአስተዳዳር ስነ-ስርዓት ሕግ ወጥ በሆነ መልኩ እንዲፈፀም ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ሰነዶቹን ለተለያዩ የፌደራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት እንዲሁም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደሚሰራጩ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ የሽግግር ፍትሕ ፖሊስ እና የፖሊሲው ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ መታተሙ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ምዕራፍን በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ድርጅቱ በቀጣይም ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል::