የሴቶችና ህፃናት ጥቃት አስከፊነት ዙሪያ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግና ድርጊቱን ለመከላከል ብሎም ምላሽ ለመስጠት ያለመ መድረክ ተካሔደ

Forum Held to Raise Awareness and Address Violence Against Women and Children

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች ሕፃናትና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ የውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ጾታዊ ጥቃትን ምክንያት በማድረግ እንደ ፍትሕ ሚኒስቴር ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችና ሕጻናትን በተለይ የህጻናት የምርመራ መዝገብ እስኪያልቅ እና ህጋዊ መጠጊያ ሲያጡ በመጠለያዎች ውስጥ እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም ተበዳዮቹ ላይ የምናደርገው ክትትል ምን ይመስላል? የጥቃቱ ሰለባዎች መጠለያ ውስጥ ካስገባን በኋላ በምን አግባብ ነው ክትትልና ድጋፍ የምናደርግላቸው? መዝገቦቻቸውንስ በልዩ ሁኔታ እያየን ነው ወይ? ካልሆነስ ቀጣይ ምን መሆን አለበት? በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ሴቶችንና ሕፃናትን አስመልክቶ ከህብረተሰቡ፣መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች አንጻር ታሳቢ ተደርጎ እንዲሁም የሴቶችና ሕፃናት ጥቃት አስከፊነት ዙሪያ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ድርጊቱን ለመከላከል ብሎም ምላሽ ለመስጠት ያስችል ዘንድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የፓናል ውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የፓናል ውይይቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከሴቶች ልማት ማረፊያ የመጡ ባለሙያዎች የመሩት ሲሆን፣ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች በባለሙያዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ኤች.አይ. ቪ.ኤድስን አስመልክቶ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዲስ መልኩ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ዳግማዊት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኤች.አይ. ቪ.ኤድስን አስመልክቶ ተቋማት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሚያስችለውን ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን አውስተው በዛሬው ዕለት ይህንንም ጉዳይ አስመልክቶ የፓናል ውይይቱ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

በመቀጠልም “ሰብዓዊ መብትን ያከበረ ኤች.አይ.ቪ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መርህ ቃል የተዘጋጀውን ሰነድ በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አየለ ወልደገብርኤል በዝርዝር ቀርቦ ከቤቱ ጥያቄና አስተያቶች ተነስተው ከባለሙያው በኩል ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ መዝሙር ያሬድ የፍትሕ ስርዓቱ የጾታዊ ጥቃትን ምላሽ ከመስጠት አንጻር በሚያደርገው ሂደት ለፍትሕ ሚኒስቴር ምስክሮች የመጠለያ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ ተቋማት የምስጋናና የዕውቅና ሰርተፍኬት አበርክተውላቸዋል፡፡

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች