በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች እና ህፃናት ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀንን በፓናል ውይይት አከበረ

FDRE Ministry of Justice Women and Children's Multi-Sectoral Affairs Directorate Celebrates International Children's Day with Panel Discussion

በዓለም ለ34ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ በየዓመቱ ህዳር 11 ቀን የሚከበረው የሕፃናት ቀን ዘንድሮም ̎ለዛሬዎቹ ሕፃናት ፍቅር እና በጎነትን እናዉርስ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች እና ሕፃናት ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከሕፃናት ፓርላማ ፣ከአዲስ አበባ የሕፃናት ጥምረት እንዲሁም ከሁሉም ክ/ከተሞች ከተዉጣጡ ሕፃናት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በሸራተን አዲስ በፓናል ውይይት የሕፃናት ቀንን አክብሯል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች እና ሕፃናት ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አለምኔ የሕፃናትን መብት ከማስጠበቅ አንፃር ሕፃናትን በሚመለከቷቸው ጉዳዮች በማሳተፍ የመብቶቻቸው ጠያቂ እንዲሆኑ ማብቃት እና ግዴታዎቻቸውን በአግባቡ እንዲረዱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም የሕፃናት ፓርላማ አደረጃጀቶች እንደ ሀገር ተዘርግተው በርካታ ስራዎችን እየሰሩ በመሆኑ በዓሉን ከህፃናቱ ጋር ከማክበር ባሻገር ህፃናቱ ከፍትሕ ሚኒስቴር አንዱሁም ከፍትሕ ዘርፉ ምን አይነት ድጋፎችን ይፈልጋሉ የሚለውን በቀጥታ ከህፃናቱ ለመውሰድ በማሰብ ይህ የፓናል ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ መከላከያ መንገዶች እንዲሁም ጥቃት ለደረሰባቸው ሕፃናት የሚያስፈልጉ ድጋፎች እና ለወደፊት መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከጉዳዩ ባለቤቶች ሕፃናት ጋር ውይይት መደረጉ ጠቀሜታውን የጎላ እንደሚያደርገው ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የሕፃናት ጉዳይ የሕፃናት ቀንን ከማክበር የተሻገረ መሆን አለበት ያለው ህፃን ጆሴፍ ቴዎድሮስ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ካለው ሁኔታ አንፃር በርካታ ሕፃናት የመማር እና የመኖር መብታቸው ጥያቄ ውስጥ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብሏል ፡፡

በተያያዘም ለወደፊት መሻሻል አለባቸው በሚል ህፃናቱ ካቀረቧቸው ሀሳቦች መካከል በሕግ አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች፣ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ዘመኑን የዋጀ ባለመሆኑ መሻሻል አለበት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ህፃናቱ ከሀገር ውስጥ ባለፈ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ስራዎችን ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው እና ለዚህም ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቁ ሲሆን በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

በቀጣይ ሕፃናትን በሚመለከት ለሚከናወኑ ሰራዎች ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ ሕፃናት የተመረጡ ሲሆን በውይይቱ ወቅት ለታዩ የመረጃ ክፍተቶች ወ/ሮ ዳግማዊት እና ዐቃቤ ሕግ ፍቅር አለም ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡

Tagged Under: ababa addis addis ababa Advocacy affairs child Child Abuse child participation Child Protection child welfare children's Children's Rights Criminal Code day Discussion international Juvenile Justice Legal Gaps multi-sectoral approach panel panel discussion parliament protection Rights Stakeholder Engagement welfare women women and children's affairs
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች