የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበር በጋራ በሚያገናኟቸው ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

FDRE Ministry of Justice and Ethiopian Lawyers with Disabilities Association Sign Memorandum of Understanding for Joint Collaboration on Common Issues

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሀን ስምምነቱን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ እንደአዲስ ከተደራጀ በኋላ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አውስተው ፍትሕ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ውስጥ የሁሉም አካል ጉዳተኞች መብቶች የተከበረበት ፍትሀዊና ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ፣ የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲስፋፋ፣ እንዲጠበቅና እንዲከበር፣ በፍትሕ ስርአቱ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲያድግ ያለመ ስምምነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ተቋማችን ስምምነቱን ለመተግበርና አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ወርቁ በበኩላቸው የዛሬው የመግባቢያ ስምምነት የፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበር አንድ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች በተለይ በአካል ጉዳተኞች መብቶች ዙሪያ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ መፍጠር፣ ለአካል ጉዳተኞች ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጠት፣ በተለያዩ የሕግና ፖሊሲ ረቂቅ ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊ ማድረግ፣ በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ሰራተኞችን መብት ማስጠበቅ፣ በተቋሙ የሚከናወኑ ተግባራት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካተው እንዲተገበሩ ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሙሴ ጥላሁን በበኩላቸው ይህን ስምምነት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ማድረጋችን ትልቅ አጋጣሚ ነው ካሉ በኋላ የዛሬው እለት ማህበራችን በመንግሥት ደረጃ ትልቅ ዕውቅና ያገኘበት ቀን እንደሆነ መግለፅ እንወስዳለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ከምንም በላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ለአካል ጉዳተኞች ባይተዋር አለመሆኑን ብዙ ጉዳተኞች ፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ እንዳገለገሉና በማገልገል ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ ተቋሙ ለአካታችነት አዲስ እንዳልሆነ ጠቁመው ይህንን ስራ በአንድ ደረጃ ከፍ አድርገን በጋራ እንሰራለን ሲሉ አውስተዋል፡፡

ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስቴርን ወክለው ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሀን እና አቶ ሙሴ ጥላሁን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዘዳንት ፈርመዋል፡፡

Tagged Under: accessibility • aid • association • Capacity Building • civil liberties • disabilities • disability • disability inclusion • disability rights • fundamental rights • Human Rights • inclusive • institutional • Institutional Reform • Justice • Lawyers • legal • Legal Aid • legal framework • Legal Profession • memorandum • Memorandum of Understanding • persons • persons with disabilities • policy reform • Rights • understanding
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች