የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል የሚያስችል በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና ክርክር ሂደት ላይ በጋራ የሚተገበሩ ጉዳዮችን በተሻለ ቅንጅት እና ውጤታማነት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ታሕሳስ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
በትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያሥላሴ በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚደረገው የጋራ ስምምነት በወንጀል ምርመራ እና ክስ ሂደት ላይ የሚኖረውን የተልዕኮ አፈጻጸም ከማቀላጠፍ ባለፈ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ሲሆን ከወዲሁ በቅንጅት የመስራት ሂደቱን በመጀመር የስራ አፈፃፀሙንም እየገመገሙ መሄድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት ለአንድ አላማ የሚሰሩ ተቋማት በመሆናቸው እንዲሁም ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የፍትሕ ጥያቄዎች በተናጠል ምላሽ መስጠት ስለማይቻል ተቀናጅቶ በጋራ መስራቱ አገልግሎቱን የተሟላ የሚያደርገው መሆኑን ጠቅሰው፤ በስምምነቱ መሰረት ለመስራት እና ውጤት ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በስምምነት ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሐር እና የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ሌሎች አመራሮቸ ተገኝተዋል።