የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ አፈጻጸምን ለማጥናት የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

Experts Committee Reviews Implementation of Civil Society Organizations Proclamation

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው የሚመራውና ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከናዎኑ የሕግና ፍትሕ ማሻሻያ ስራዎችን አፈጻጸም ለመከታተል ከተቋቋሙት የባለሙያዎች ኮሚቴ ውስጥ አንዱ የሆነው እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ/ አዋጅ ቁጥር 1113/2011/ አፈጻጸምን የሚያጠናው ኮሚቴ ለጥናቱ የሚያግዝ የግብአት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ ከተማ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን የህጎች አፈጻጸም ላይ ያሉ ችግሮችን ለመለየት ያለመ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው አማካሪ የሆኑት አቶ አምደሚካኤል ጌታቸው እንደተናገሩት አዋጁ በተሻለ ደረጃ የዜጎች የመደራጀት መብትን በማስጠበቅ ረገድ ብዙ አስተዋጾዎችን ማድረጉን ተናግረው፤ በአፈጻጸሙ ላይ ደግሞ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚነሱ ጠቁመዋል፡፡ የመድረኩ ዋና ዓላማም አዋጁ ምን ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣ፣ ምንስ ጉድለቶች እንዳሉት፣ በተለይ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አንጻር የሚነሱ ችግሮች ምንድን ናቸው? ችግሮቹ ከየት ነው የሚመነጩት፤ ከአሠራር ነው ወይስ ከተቋማት የመፈጸም ፍላጎቶች፣ ወይስ ህጎች በተሟላ መንገድ ባለመውጣታቸው ነው የሚሉ ጥያቄዎች ምላስ እንዲያገኙ ነው ብለዋል፡፡ አማካሪው አክለውም በመድረኩ አዋጁ በራሱ ክፍተቶች ያሉበት ስለመሆኑ ወይስ አዋጁን ለማስፈጸም የሚያግዙ የአደረጃጀትና የአሠራር ስርዓቶች በበቂ ስለመዘርጋታቸው ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ አቶ አምደሚካዔል ንግግራውን ሲያጠቃልሉ በአዋጁ ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በህ አፈጻጸም ዙሪያ ምን አይነት ምልከታ እንዳላቸው እና አዋጁን ለመፈጸምስ በተጨባጭ ችግር እየፈጠሩ ያሉ ምክንያቶች ምንነት ላይ ያላቸውን ሃሳቦች አንስተው ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የአማካሪውን ንግግር ተከትሎ የጥናት ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ቁምላቸው ዳኜ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ የመደራጀት መብትን የሚገድብ፣ ለኤጀንሲው ትልቅ ሥልጣን የሚሰጥ፣ የፍርድ ቤት ይግባኝ መብቶችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የገንዘብ ምንጭ የሚገድብ ነበር ብለዋል፡፡ ሰብሳቢው እንደገለጹት ይህንኑ መሠረት በማድረግ አዲሱ አዋጅ ሲወጣ የመደራጀት ህገ-መንግስታዊ መብትን በሰፊው ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንደወጣ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መመዘኛዎች ጋር የተጣጣመ እንደሆነና፤ በተቻለ መጠን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶን በፋይናንስም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እድል የሰጠ መሆኑን በመነሻ ሀሳባቸው ላይ አካተው አቅርበዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ባለስልጣኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን ለይቶ በሪፖርቱ ላይ ማካተቱን ገልጸው አዋጁ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ሰፊ መፈላለግን እንዲሁም ትብብርንና መልካም ግኝኙነትን መፍጠሩ፣ ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የአገልግሎት አሰጣጦች መሻሻላቸውን እና በአሁኑ ጊዜ አፈጻጸሙ 93.3% መድረሱን፤ የአገልግሎት አሰጣጡ ከማንዋል ወደ ኢንተርኔት አገልግሎት መለወጡ እና ከምልልስ ነጻ መሆኑ፤ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የተስተዋሉ ጠንካራ ጎኖች ናቸው ብለዋል፡፡

የሕግ አማካሪው በተጨማሪም ብልሹ አሰራሮች መቀነሳቸው፣ ተቋሙ ራሱ ችግር ፈች ተቋም መሆኑ፣ ቅንጅታዊ አሰራሮች መጠናከራቸውን በበጎ ጎን አንስተው በማሳያነትም በፌዴራል እና በክልል መንግስታት እንዲሁም በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ 4 የሚሆኑ ጉባዔዎች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር መፈጠሩ፣ የመደራጀት መብት መረጋገጡን ያነሱት አቶ ተስፋዬ አዋጁ ከወጣ በኋላ 2050 የሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን፣ ወደ 1800 ለሚጠጉ ነባር ድርጅቶች ደግሞ ዳግም ምዝገባ መደረጉ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የሚስተዋሉ ጠንካራ ጎኖች ናቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ድርጅቶቹ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መጀመራቸውን፤ እንዲሁም በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን 15 የሚሆኑ መመሪያዎች ተረቀው 4 የሚሆኑት በቦርድ ጸድቀው በፍትሕ ሚኒስቴር የመመሪያ ቁጥር ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውን፤ 5ቱ መመሪያዎችም ለፍትሕ ሚኒስቴር መላካቸውን፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መቋቋሙ ሌላኛው የአፈጻጸም ጥንካሬዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ባለስልጣኑ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ እንደተግዳሮት ብሎ ያስቀመጣቸው ጉዳዮችን በተመለከተ በሀገሪቱ ተሰማርተው ከሚሰሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከግልጽነትና ተጠያቂነት ጋር የተያያዙ ጥቆማዎች አልፎ አልፎ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መቅረባቸው፣ ህጉ እስከታች አለመውረዱንና የክልሎች ሕግ እስካሁን ጸድቆ ወደ ስራ አለመግባቱ፣የባለስልጣኑ በጀትና የሰው ኃይል ውስንነቶች መኖር፣በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭት አዋጁን ተደራሽ እንዳይሆን ማድረጉ፣ እንደ ዓለም የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝም በአገራችን መከሰት በአዋጁ አፈጻጸም ላይ እንደ ተግዳሮት ሆነው መቀመጣቸውን አቶ ተስፋዬ ባቀረቡት ገለጻ ላይ ተመላክቷል፡፡

በክቡር የመንግሥት የሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው የተቋቋሙት የባለሙያዎች ኮሚቴዎች የአፈጻጸም ጥናቱን የሚያደርጉባቸው 9 ህጎች ላይ ሲሆን እነሱም የአስተዳር ስነ-ስርዓት ህጉን፣ የሽብር ህጉን፣ በሰው የመነገድና ሰዎችን ህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጁን፣ የንግድ ህጉን፣ የሚዲያ ህጉን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጁን እና የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዋጁ ላይ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ጽሁፎቹ ከቀረቡ በኋላ ከመድረኩ ለጥናት ኮሚቴው ግብአት የሚሆኑ የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ የእለቱ መርኃ-ግብር ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Civil Society Organizations • Expert Committee • Legal Implementation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች