የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማህበር በህጋዊ መቋቋም እና ምስረታው ማግስት ባዘጋጀው የመተዳደሪያ ደንብ እና የተለያዩ መመሪያዎች ረቂቅ ሰነድ ላይ ግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ አካሄደ

Ethiopian Federal Lawyers Association Holds Consultation Forum on Draft Regulations and Guidelines

ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የእለቱን የምክክር መድረክ በንግግራቸው እንዲከፍቱ ለፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታው ግብዣ ያቀረቡት የማህበሩ ፕሬዘዳንት ወ/ሮ ስንዱ አለሙ ሲሆኑ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ የሆኑት አቶ አለምአንተ አግደው በመልዕክታቸው ጠበቆች በፍትሕ ስርዓት ውስጥ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት በመሆናቸው ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እድገት የሚያበረክቱትን ሚና በተሻለ እንዲጎለብት ሙያውን ማሳደግ የግድ የሚል ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ሙያውን ከማሳደግ አንጻርም የፌዴራል ጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 ወጥቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በአዋጁ መሠረትም ታሪካዊውን እና የመጀመርያውን ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ ሁሉንም ጠበቆች የሚያቅፍ የፌዴራል ጠበቆች ማህበር ተመስርቷል፤ ብሎም አመራሮቹን መርጧል ያሉት አቶ አለምአንተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እና በመደገፍ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ ከድጋፉ መካከልም የመገልገያ ቢሮ፣ የሰው ኃይል፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የስራ ማስኬጃ በጀት እንደሚገኙበት አንስተው በውስጠ ደንብ እና መመሪያ ዝግጅትም ላይ ለማህበሩ ሙያዊ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ማህበሩ በቀጣይ እራሱን አሳድጎ የተጣለበትን ኃላፊነት በራሱ መወጣት እስኪችል ድረስ ድጋፉ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠው በሰነድ ዝግጅቱን እና መድረኩን ላዘጋጁ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም የማህበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ሰነድ ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ በገለጻው የተቋሙን ዋነኛ መዋቅሮችና አደረጃጀቶች፣ የአመራር አካላትን አሠራር እና አደረጃጀት፣ የስራ ዘመን እና መሰል ቁልፍ ጉዳዮች ስለሚመሩበት ሁኔታ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ አክለው ረቂቅ ደንቡን ለማዘጋጀት የኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፖ ሀገራት የጠበቆች ማህበር አደረጃጀቶችና መዋቅራዊ ተሞክሮዎችን በጥልቀት በማጥናት የጠበቆች ማህበር በአህጉሩም ሆነ በአለምአቀፍ ደረጃ ደረጃውን የጠበቀ አደረጃጀት እንዲኖረው ሙከራ የተደረገበት ነው ብለዋል::

በተጨማሪም በአዋጅ ቁ.1249/2013 መሠረት የሚደራጁት ሶስት ኮሚቴዎች የአሠራር ስርዓት መመሪያዎችን ጨምሮ 5 ረቂቅ መመሪያዎች ተዘጋጅተው በመድረኩ የቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ እና በቀጣይ በጽሑፍ የሚቀርቡ ሀሳቦችን በማካተት እንዲሁም አቅም በፈቀደ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ረቂቁን በማዳበር እና በማፀደቅ ወደ ስራ የማስገባት ሥራ እንደሚሰራ ከመድረኩ ተገልጿል፡፡

Tagged Under: Legal Regulations
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች