ሴቶች እና ህፃናትን አስመልክቶ በክልሎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ዙሪያ ውይይት እተካሄደ ነው

Discussion Underway on Activities Related to Women and Children Being Implemented in the Regions

በኢ.ፌ.ዳ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በክልሎች ሴቶች እና ሕፃናትን አስመልክቶ ያሉ ህጎች ተፈፃሚነት፣ መረጃ አያያዝና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲሁም ያለ እድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በአዳማ ከተማ ከሰኔ 8-9 2015 ዓ.ም የሚቆይ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በኢ.ፌ.ዳ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አለምኔ እንደገለጹት እንደ አገር በፌደራል እና በክልል ጉዳዮች መካከል እየተጠናከረ ያለውን በጋራ የመሥራት ጅማሮ ለማጠናከር ፍትሕ ሚኒስቴር እና ሁሉም የክልል ፍትሕ ቢሮዎች ስራዎችን በጋራ በመሥራት አንድ ላይ የተጠቃለለ ሪፖርት እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ተመሳሳይ የሥራ ክፍሎችም ግንኙነት ፈጥረው ተመሳሳይ አደረጃጀት እና የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የምንተጋገዝበት መድረክ ያስፈልገናል ያሉት ዳይሬክተሯ ይህም ተጠናክሮ እየቀጠለ በመሆኑ የዚህ አንድ አካል እንደመሆናችን በክልሎች ከሴቶች እና ሕፃናት አንፃር ያለው አደረጃጀት ምን ይመስላል? ምን አይነት ስራዎች መሰራት አለባቸው? እንዴት መጠናከር አለብን? የሚለውን ለመወያየት እንደ መነሻ ይሆነናል በሚል በሁሉም ክልል ፍትሕ ቢሮዎች ሴቶች እና ሕፃናት ዙሪያ ያለውን አደረጃጀት አውቀነው ልምድ እንድንለዋወጥ እና ለ2016 ዓ.ም ውጤታማ ስራ ለመሥራት ይህ የውይይት መድረክ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ከክልሎች የመጡ ተወካዮች በ2015 ዓ.ም ሴቶች እና ሕፃናትን አስመልክቶ ያላቸውን አደረጃጀት፣ የህጎች ተፈፃሚነት፣ መረጃ አያያዝና ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ፣አስገድዶ መድፈር እና ጠለፋን ለማስወገድ በተከናወኑ ተግባራት የአንድ ማዕከል አገልግሎት (One stop center) እንቅስቃሴን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በቀረቡት ሪፖርቶችም የበጀት እጥረት በሁሉም ክልሎች እንደ ችግር የተነሳ ሲሆን የሰላም ችግር በነበረባቸው አንዳንድ ክልሎች ደግሞ ማህበረሰቡ በሕግ እምነት በማጣቱ ምክንያት ጥቃት ሲደርስ ወደሕግ ያለማምጣት ችግር እንዳለ ተመላክቷል፡፡

የውይይት መድረኩ በነገው ዕለትም የሚቀጥል ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት እና በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ሪፖርት ቀረቦ ውይይት የሚካሄድና ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተጠቁሟል፡፡

Tagged Under: budget constraints • bureaus • Capacity Building • child • child marriage • children • data management • federal • federal ministry of justice • female • female genital mutilation • gender-based • Gender-Based Violence • genital • Human Trafficking • inter-agency coordination • Justice • Legal Awareness • Legal Frameworks • Marriage • ministry • mutilation • one stop center • Policy Implementation • Rape • Regional • Regional Justice Bureaus • sexual assault • women
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች