ፍትሕ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ግብአት ለማሰባሰብ የሚያስችል ዉይይት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከተወከሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር በሪፎርም የማሻሻያ ከተደረገባቸዉ ህጎች አንዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ነዉ ያሉት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ፤ አሁን የቀረበው ማሻሻያ ረቂቅ የተዘጋጀው በርካታ ጥናቶች ከተደረጉ በኋላ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዱኤታው አክለውም ማሻሻያው ያስፈለገው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል፣ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር ፤በዘርፉ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ የሕዝብና የአገርን ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ እንደሆነ ጠቁመው፣ ከመድረኩ ተሳታፊዎች የሚገኘዉ ግብአት ለሚደረገዉ ማሻሻያ ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፤ ማርቀቅ፤ማረምና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት በበኩላቸዉ አዋጁ የወጣዉ ከስድስት ዓመታት በፊት እንደነበረ አስታዉሰዉ ባለፉት አመታት በአፈጻጸም ወቅት አጋጥመዉ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመቀነስ አዳዲስ መብቶችን በማካተት ዘርፉን ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ማሻሻያ ረቂቁ መዘገጀቱን ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል፡፡
በዉይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች የአዋጁ የማሻሻያ ረቂቅ ላይ ጥቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች በመድረኩ አወያዮች አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡