በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ የአካል ጉዳተኞችን ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠና ችግሮቻቸውን ፈትቶ የስራ ውጤታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ በተቋሙ ላሉ የስራ ክፍል አመራሮች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የጥናቱን መቅረብ አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ አምደሚካኤል ጌታቸው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ስራቸውን ከማንኛውም ተጽእኖ ከሚያሳድርባቸው ሁኔታ ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ለማስማስቻል ጥናት መደረጉ ተገቢ እንደሆነ ገልጸው በጥናቱ የተገኙ ክፍተቶችን በደንብ ፈትሾና አረጋግጦ የሚስተካከልበትን እድል በመፍጠር ለአካል ጉዳተኞች አመቺ የስራ አካባቢና ሁኔታ እንዲፈጠር ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህጻናትና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ወ/ሪት ምዕራፍ ተስፋየሱስ እንደገለጹት በተቋሙ ካሉ አካል ጉዳተኞች ቁጥር አንጻር ጥናት ተደርጎና ትኩረት ተሰጥቶ የችግሮቹን መነሻ በማወቅና በመፍታት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ በመሆኑ የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ጥናት መደረጉን አውስተዋል፤ አያይዘውም በጥናት ላይ የተመሰረቱ ችግር የመፍታት ዘዴዎችን መጠቀም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠርም በላይ ለተቋሙ ስራ መሳካት ቀላል የማይባል አስተዋጾ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ በተቋሙ ያሉ አካል ጉዳተኞችን መሠረት አድረጎ የተሰራ ሲሆን ከስራ ሁኔታ ምቹነት፣ ከሕንጻ ግንባታ፣ ከመስሪያ ክፍል ቢሮዎች፣ ከትራንስፖርት፣ ከመኖሪያ ቤት ችግር፣ ከትምህርት እና ሥልጠና ቅድሚያ እድል ማግኘት፣ ለአካ ጉዳተኞች አመቺ የስራ ቁሳቆሶችን ከማሟላት አንጻር፣ የረዳት አንባቢዎች አመላመል እና መሰል ጉዳዮች በጥናቱ እንደ ችግር የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያስቻላሉ ተብለው በጥናቱ የተቀመጡ አመላካች ሀሳቦችንም ወ/ሪት ምእራፍ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የቀረበውን ጥናት ያወያዩት የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እና ፕሮጀክት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ኖህ ታከለ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ ጥናት መደረጉ አግባብነት ያለው መሆኑን ገልጸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፤ በቅድሚያ የችግሩን መንስኤ ማወቁ ለመፍትሄው አንድ እርምጃ መቅረብ እንደሆነ ጠቅሰው በቀረበው ጥናት አጠቃላይ አስተያየት እንዲሰጥበት የውይይት መድረኩን ክፍት አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ ጥናቱ የበለጠ ዳብሮ ከተቋም ያለፈና በሌሎች ተቋማት ያሉ አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ማጥናት ቢቻል እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸው ህጎችና መመሪያዎችም ተሻሽለው ለአሠራር አመቺ የሚሆኑበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ ይሆናል የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡