የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ላይ በተደረገ ጥናት እና ጥናቱን መሰረት ተደርጎ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተካሄደ

Discussion Held on Draft Proclamation Based on Study of Criminal Witnesses and Informants Protection Proclamation

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ምስክሮችና ወንጀል ጠቋሚዎች ጥበቃ ዳሬክቶሬት በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 699/2003 ለማሻሻል ባደረገው ጥናትና እንዲሁም በጥናቱ መነሻነት በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር መካከለኛ አመራሮች ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብሎም ህብረተሰቡ በህጉ ላይ ያለውን እምነት ጠብቆ ትብብር ማድረግ የሚያስችልና በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቢሆንም በትግበራው ላይ የተለያዩ ችግሮች ያሉበትና የምስክርነት ግዴታን ለመወጣት የማያስችሉ ሁኔታዎች ያሉበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በትራንስፎርሜሽን እቅዱ የወንጀል ጠቋሚዎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ቁልፍ ሚና የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስታውሰው እየተሰራበት የቆየው አዋጅ በምስክሮች አያያዝ ረገድ አፈፃፀሙ ምን ይመስል እንደነበር፣ ከተለያየ አካባቢ ለሚመጡ ምስክሮች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን አሟልቶ ከማስተናገድ አንፃር ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዞ መነጋገር አስፈላጊ በመሆኑ የመድረኩ ተሳታፊዎች በአዋጁ ስላልተሸፈኑ ጉዳዮች፣ ከስራ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ አካላት አንፃር ስለሚያጋጥሙ ችግሮች በማንሳት ጥልቅ የሆነ ውይይት በማድረግ አዋጁ የበለጠ ለሕግ የበላይነት መከበር አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ማድረግ ስለሚያስፈልግ በንቃት እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

በመቀጠል በስራ ላይ የሚገኘው የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ያሉበትን ክፍተቶች በማስመልከት የተደረገው ጥናት የቀረበ ሲሆን፤ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች የተመለከቱትን በወንጀል ጉዳዮች የመመስከር ግዴታ ያለባቸው ቢሆንም በቅድሚያ የራሳቸው፣ የቤተሰቦቻቸው ወይም የንብረታቸው ደኅንነት በሕግ አግባብ ሊጠበቅና ዋስትናም ሊሰጣቸው እንደሚገባ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በዚህ ረገድ የምስክሮችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እየተሰራበት የሚገኘው አዋጅ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ከወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚሄድና ዓለም ዓቀፍ የሀገራትን የምስክሮች ጥበቃ መስፈርት የሚያሟላ አዋጅ ማዘጋጀት በማስፈለጉ ጥናት ተደርጎ በጥናቱ መሠረት የሕግ ክፍተቶችን የመለየት ስራ መከናወኑ ተገልዖል፡፡

ነባሩን አዋጅ ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለውይይት እንዲቀርብ ሲደረግም በጥናት የተለዩና በስራ ላይ ክፍተት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በማጋጠማቸው ሲሆን ነባሩ አዋጅ ለአብነት ያህል አዋጁን የማስፈፀም ሥልጣንን ለማን እንደተሰጠ በግልፅ ያልተለየበት፣ ግዛታዊ የተፈፃሚነት ወሰንን የማያመለክት፣ የሰው ኃይል ስብጥሩን ከጥበቃ አካላት ሁኔታ ጀምሮ፣ የስነ ልቦና፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወዘተ ሚና በዝርዝር ለይቶ የማያመለክት፣ የበጀት፣ የምስክሮች ጥበቃ ሚስጢራዊነት እና ተያያዥ ጉዳዮችን ያላካተተ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

እነዚህን የሕግ ክፍተቶች በመሙላት የምስክሮችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል አዋጅ ማዘጋጀት እንዳፈለገ በውይይቱ ወቅት የተመላተ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በጥናት የተለዩ ጉዳዮች ተካተውበት የተዘጋጀው የወንጀል ምስክሮች እና የጠቋሚዎች ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀሎች ዳሬክቶሬት አማካኝነት ቀርቦ በዝርዝር ገለፃ ተደርጎበታል፡፡

በመጨረሻም በቀረበው ጥናትና በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች ከስራው ጋር ተያይዞ ከሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎችና ካላቸው ልምድ በመነሳት ለረቂቅ አዋጁ በግብዓትነት የሚጠቅሙ ሀሳብና አስተያየቶችን በመስጠት የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Criminal Justice Legal Reform Witness Protection
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች