የማህበረሰብ የፍትህ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በሲዳማ ክልል በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ ቱሎ ቀበሌ ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀመረ

Community Justice Service Center Officially Launched in Sidama Region, Hawassa Tulla Sub-City, Tulo Kebele

የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በሲዳማ ክልል በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ ቱሎ ቀበሌ እና በወንሾ ወረዳ አቦ ወንሾ ባህል ማዕከል በመገኘት የማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል እና ባህላዊ የ”አፊኒ ሶንጎ” ማቋቋሚያና እውቅና መስጫ መርሀ ግብር በይፋ አስጀመሩ::

በሀገር ደረጃ በፍትሕ ዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የ3 ዓመት የፍትሀ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አቅድ ፍኖተ ካርታ በትግበራ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በፍኖተ ካርታው ከሚተገበሩ አምዶች ውስጥ አንዱ “የመሰረተ ማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎትን ማሳደግ” አንዱና ዋነኛው ነው። ይህን አምድ ገቢራዊ ለማድረግ የፍትሕ ሚኒስቴር በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ክልሎችም በክልላቸው የሚገኙ የመሰረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ ይችሉ ዘንድ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

የዚህ ጥረት አካል ሆኖ የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) በሲዳማ ክልል በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ ቱሎ ቀበሌ እና በወንሾ ወረዳ ወረዳ አቦ ወንሾ ባህል ማዕከል በመገኘት የማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከልን የሲዳማ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቶ ማሩ ፣ የሄግ ኢንስቲትዩት ተወካዮች፣ የክልሉ ባህል፣ቱርዝም እና እስፖርት ቢሮ አመራሮች፣ የሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ እና ወንሾ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችና አመራሮች ፣ የወንሾ ባህል ማእከል ‘ጋና’፣ ከቀበሌያት የተወጣጡ የሀገር ሽማግለዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።

በዚህ መርሀ ግብር ላይ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ባስተላለፉት መልዕክት “አፊኒ” የሲዳማ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የሲዳማ ሕዝብ የተጣሉ ወገኖችን ለማስማማትና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀምበትና ከአባቶች ወደ ልጆች ሳይበረዝ እየተላለፈ የቆየ ሥርዐት መሆኑን አውስተው በአሁኑ ወቅት በመደበኛነት አገልግሎት ላይ እንዲውል የክልሉ ምክር ቤት ባፀደቀው አዋጅ መሠረት ”አፊኒ” ዛሬ በይፋ ወደ አገልግሎት መግባቱ ለፍትሕ ሥራዓቱ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብሏል። በተለይ የ“አፊኒ” ባህላዊ ዳኝነት ስርኣት ግጭቶችን ለመፍታት፣ ማኅበራዊ መስተጋብርንና አብሮነትን ለማጠናከርና ሰላምን ለማፅናት ጉልህ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ቱባ ማኅበራዊ እሴት መሆኑን አንስተዋል።

ዶ/ር ኤርሚያስ አክለውም ይህ ቱባ ባህልና ማኅበራዊ እሴት የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አምድ የሆነውን የመሰረተ ማህረሰብ ፍትሕ አገልግሎት በክልሉ ገቢራዊ ለማድረግና መደበኛውን የፍትሕ ስርዓት ለመደገፍ ሁነኛ ስርዓት መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶችን በሕግ እውቅና በመስጠት መደበኛውን የፍትሕ ሥርዓት ሳይተኩ የማገዝ ሚናቸው እንዲወጡ ፍትሕ ሚኒስቴር በርካታ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን በመግለጽ የዚህ መሰረተ-ማኅበረሰብ ፍትሕ ማዕከልን በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ ቱሎ ቀበሌ በመገኘት መክፈት መቻሉና ለማዕከሉ የተደረገ የግብዓት ድጋፍ የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ብሐራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ማቶ ማሩ በበኩላቸው ከዛሬ ጀምሮም በክልሉ በ656 ቀበሌያት እንዲሁም በ44 የወረዳና ከተማ መዋቅሮች ላይ የ”አፊኒ” ሥርዓት መዋቅር ተዘርግቶለት በባህላዊ ሽማግሌዎች አማካኝነት የዳኝነት አገልግሎት ይሰጥበታል በማለት አሳውቋል። በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴርን እና The Hague Institute for Innovation of Law (HIIL) ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

የሲዳማ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ከዚህ በፊት ይህን የባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ሲያከናውኑ ምቹ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውንና በግብዓት ችግር ምክንያት አገልግሎቱን በሚፈለገው ደረጃ መስጠት ተቸግረው እንደነበር ገልፀው አሁን ባገኙት ድጋፍ ችግራቸው በዘላቂነት እንደሚቀርፉላቸው ገልጸዋል። የአፊኒ ባህላዊ ስርዓቱንና እሴቱን ጠብቀው ለማህበረሰቡ ተገቢውን ፍትሕ መስጠታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥለው ገልፀዋል።

ይህ ለክልሉ የፍትሕ ስርዓት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የሚታሰበው ማዕከል እውን ሊሆን የቻለው The Hague Institute for Innovation of Law (HIIL) ከተባለ የኔዘርላንድ ድርጅት እና ዴስትኒ ኢትዮጵያ በተገኘ የቴክኒክ እና የግብዓት ድጋፍ ነው።

Tagged Under: Access to Justice Capacity Building center community community-based justice Conflict Resolution customary law hawassa hiil Justice Justice Sector Transformation kebele Legal Reform region rural justice Service sidama Sidama Region the hague institute for innovation of law traditional traditional dispute resolution
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች