የፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ-ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ከፍትሕ ለሁሉም (Justice for All – Prison Fellowship Ethiopia) ጋር በመተባበር ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መካከለኝ አመራሮች በአመራርነት እና በስብአዊ መብቶች ዙሪያ የአቅም ግንበታ ሥልጠና በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በፍትሕ ለሁሉም ተቋም ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት አቶ ውብሸት ክብሩ በሥልጠናው እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ወቅት እንደተናገሩት ፌሎሽፑ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየስራ እንደሆነና በተለይም በሽግግር ፍትሕ ላይ ለመሥራት በዝግጅት ላይ እንዳለ ጠቁመው ይህን መሰሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠና የትብብሩ አንድ አካል መሆኑን አውስተዋል፡፡
የፍትሕ ዘርፉን የሰው ሃይል የአቅም ማጎልበት ስራዎችን በመሥራት እንዲሁም የሚሰሩ ስረዎችን በቴክኖሎጂ የተደገፉ በመድረግ መደገፍ አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንበታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ይህንን ለማሳካት ከቅጥር ጀምሮ የሰው ሃይሉን በማብቃት እንዲሁም የተለያዩ አስራሮችን በመዘርጋት ጥቅማ ጥቅሙን ማስጠበቅ ይገባል በማበለት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በፍትሕ ዘርፉ ላይ ያለው የሰው ኃይል ላይ ትኩረት አድርገን ስንሰራ ነው ያሉ ሲሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት የሪፎርምና የተቋም ግንበታ ትኩረት ያደረገው የሰው ሀብት፣ የአሠራር ሥርዓት እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ በመሆኑ መሰል ሥልጠናዎች በቀጣይ ወደ ክልል ፍትሕ ቢሮዎችም ጭምር መሰጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የዛሬውን ሥልጠና የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ሲሆኑ ሥልጠናው ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡