የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በመረጃ አያያዝ፣በመዝገብ አደረጃጀት ፣ቅብብሎሽ እና አሠራር ሁኔታን አስመልክቶ በተጠናው ጥናት መሠረት በተዘጋጀው የሬጅስትራር አተገባበር ማኑዋል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ግንቦት 12 እና 13/2017 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡
በሥልጠና መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ሲመሌ ጉተማ፤ ዘርፉ ከሚያከናውናቸው በርካታ ስራዎች ውስጥ ዋነኛው ስራ ከመዝገብ ጋር የሚያያዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀልጣፋ፣ ተገማች እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት ፣ከመዝገብ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በዘርፉ የሬጅስትራር የስራ ክፍል መቋቋሙን እና የአሠራር ማኑዋል ተዘጋጅቶ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን ገልፀው፤ ሥልጠናው ቀደም ሲል ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት ስራዎች በማዕከል ሲሰሩ በምን መልኩ መሆን እንዳለባቸው ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠናው በስራ ክፍሉ ሀላፊዎች አማካኝነት ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተወጣጡ ሰራተኞች የተሰጠ ሲሆን በጥናቱ እንደችግር የተለዩ ጉዳዮችን ለመቅረፍ ስራዎችን ቀልጣፋ ፤ውጤታማ ፤ወጪ ቆጣቢና ዲጂታላይዝ ለማድረግ፤ እንዲሁም ስራዎችን ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚያመች ሁኔታ ከመምራት አንጻር ፤ጥራት ያለው የመረጃ አያያዝ፣ ቀልጣፋ የመዛግብት ቅብብሎሽን ከመዘርጋት እና የመዛግብት ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር በማኑዋሉ የተቀመጡ ዝርዝር የአሠራር መርሆች ተዳሰዋል፡፡