የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር እ.ኤ.አ. ጁላይ 31 ቀን 2023 በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገው ስምምነት፣ ከህዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና መንግስት ጋር እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 05 ቀን 2024 የተፈረሙት በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር እና ፍርደኛ የማስተላለፍ ስምምነቶች እንዲሁም ከብራዚል ፌደራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ጋር እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 11 ቀን 2024 የተፈረመው ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ታህሳስ 14 ቀን 2018 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ወቅት ፀድቀዋል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቻይና እና ከብራዚል ጋር ያላት ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ የሚገኝ ነው፡፡ አገራቱ የብሪክስ አባል በመሆናቸው ጭምር በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ እና ወደፊትም የበለጠ እየጎለበተ እንደሚሄድ የሚጠበቅ ሲሆን ይህ በንግድና በኢንቨስትመንት ያለው ግንኙነት በሕግና በፍትሕ ዘርፎች እንዲደገፍና የበለጠ እንዲጠናከር ለማድረግ በሕግ ነክ ጉዳዮች ስምምነቶች መደረጋቸው አስፈላጊ ነዉ፡፡
ከዚህ አንጻር እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ስምምነቶች በእንካ ለእንካ መርህ (በሰጥቶ መቀበል አግባብ) መሰረት ከሚካሄዱ ትብብሮች ባለፈ ከደቡብ አፍሪካ ጋር አሳልፎ ለመስጠት በሚያበቃ የወንጀል ድርጊት (Extraditable Offences) ምክንያት ለክስ ወይም ቅጣት እንዲፈጸምበት በሁለቱ አገራት የሚፈለግን ግለሰብ አሳልፎ ለመስጠት፣ ከቻይና ጋር በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና የክርክር ሂደት ላይ ባሉ ጉዳዮች ሚፈለጉ ማስረጃዎችን እና መረጃዎችን የመስጠት እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን የመያዝ፣ የማገድ እና የመዉረስ ተግባርን ለማከናወን፣ እንዲሁም ከቻይና እና ከብራዚል በተስማሚ አገራት ውስጥ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍርደኞች ቀሪ የእስራት ጊዜያቸውን ወደየአገሮቻቸው በመዘዋወር ቀሪ የእስራት ጊዜያቸውን መፈፀም እንዲችሉ የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
የስምምነቶቹን አፈጻጸም በሚመለከት የስምምነቶቹ ይዘት ከወንጀል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚደረግ ዓለም አቀፍ ትብብርን እንደመሆናቸው የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40(1) እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (12) መሠረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር እንዲያደርግ ተግባርና ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ እንዲሁም በስምምነቶቹ ውስጥ የፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ማዕከላዊ ባለስልጣን (የስምምነቶቹን አተገባበር የሚያስተባብር አካል መሆን) የተሰየመ በመሆኑ የስምምነቶቹን ተፈፃሚነት ለመከታተል ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
ስምምነቶቹ ከአገራቱ ጋር ተደርገው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ የሚኖራቸውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት የፍትሕ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መዋዋያና ማጽደቂያ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1024/2009 መሰረት ከሚኒስትሮች ም/ቤት አስፈላጊውን ፈቃድ በማግኘት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከአገራቱ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ድርድር ተደርጎባቸው የተፈረሙ ናቸው፡፡
እነዚህ ስምምነቶች በአገራችን እንደተከናወነው ሁሉ በሌሎቹ ተዋዋይ አገራት የውስጥ ሕግ መሰረት ተገቢው ቅድመ-ሁኔታዎች ተሟልተው የፀደቁ ስለመሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ ሥራ የሚገቡ ይሆናሉ፡፡