በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳሬክቶሬት የፌደራል ባለድርሻ ተቋማትን በማስተባበር በተዘጋጀው በ3ኛው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሃ ግብር (2019-2023) ረቂቅ ሰነድ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ መድረክ ከክልል ፈፃሚ ተቋማት ተወካዮች ጋር ከጥር 14 -15 ቀን 2018ዓ.ም በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በሃገራችን ከዚህ ቀደም ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሃ ግብር ሰነድ 1ኛው ዙር ከ2003-2007 እንዲሁም 2ኛው ዙር ከ2008-2012 ተዘጋጅቶ ተግበራዊ የተደረገ ሲሆን፤ ሰነዱ እንደ ሃገር በአለም አቀፍ ደረጃ ፈርመን የተቀበልናቸውን ስምምነቶች እንዲሁም በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የተካተቱ የተለያዩ መብቶችን በተደራጀ መልኩ ማስተግበር የሚቻልበት ዕቅድ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሰነዱ አሁን ካሉት አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መስፈርቶች አንጻር እንዲሁም ከሃገራዊ ብሎም ከክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችን ተቀዳሚ በማድረግ የሚዘጋጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዚህ ደረጃ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች መዘጋጀታቸው የድርጊት መርጋሃ ግብር ሰነድ ዝግጅቱን የተሟላ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የሶስተኛው ረቂቅ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ደርጊት -መርሃ ግብር ዝግጅት ሂደትና መሰረታዊ ይዘትን በተመለከተ ለተሳታፊዎች ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ የቀረበ ሲሆን፤ በዚህም ወቅት ሰብዓዊ መብት እና የልማት እቅዶቻችን ተናበው እንዲሄዱ ለማድረ እንዲሁም አለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት የሚችል ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑ ተነስቷል፡፡
በመጨረሻ የውይይት መነሻ ሰነዱን መሰረት በማድረግ በተለይ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት እና የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች አፈፃፀም፤ በሲቪልና ፖለቲካ መብቶች፤ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች፤ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች መብቶች፤ የመርሃ ግብር ማስፈፀሚያ፣የክትትልና ግምገማ ስርዓት ዙሪያ ተሳታፊዎች በየክልሎቹ ያሉ ተጫባጭ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ ለ3ኛው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ዝግጅት የሚሆን ግብዓት ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
በግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይህን ይርጋን ጨምሮ ከአዲስ አበባ መስተዳድር፤ ከአማራ ፤ ከሐረሪ፤ አፋር፤ ሶማሌ፤ ጋምቤላ፤ ቤኒሻንጉል ክልሎች የተወከሉ የፈፃሚ ተቋማት በየደረጃው ያሉ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በቀጣይ መሰል የውይይት መድረኮች ከተቀሩት የክልል ፈፃሚ ተቋማት ተወካዮች፤ ከፌደራል ባለድርሻ ተቋማት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ተወካዮች ጋር የሚካሄድ ይሆናል፡፡
መድረኩን የፍትሕ ሚኒስቴር ከአውሮፓ ሕብረትና ሴንተር ፎር ጀስቲስ ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል፡፡