የፍትሕ ሚኒሰቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክቶሬት ከጂ.አይ.ዜድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሰብዓዊ መብቶች ክትትል ስርዓት ዙሪያ ያጠነጠነ የሁለት ቀናት ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል፡፡
በስልጠና መድረኩ 29 ሴት እንዲሁም 1 ወንድ በድምሩ 30 የፌዴራል ዐቃቤያነ ሕግ የተሳተፉ ሲሆን ፍትሕ ሚኒሰቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ክትትል ስራ ወጥነቱን በጠበቀ የአሰራር ስርዓት ለመምራት አልሞ ያዘጋጀው ማብራሪያ መጽሃፍ መሰረታዊ ይዘቶች እና ተያያዥ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በስልጠናው ተዳስሰዋል፡፡
በዚህ ስልጠና በጥልቀት ከተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ በተጠርጣሪ ማቆያ ስፍራዎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች እና ተከሳሾች መብት አጠባበቅ እና አከባበርን የሚመለከት ሲሆን ዐቃቤያነ ሕግ የግል ተበዳዮች በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ ፍትሕ እንዲያገኙ የማድረግ ተልዕኳቸውን ከመወጣት ጎን ለጎን ተጠርጣሪዎች እና ተከሳሾችም በህገ-መንግስቱ እና ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እውቅና ያገኙ መብቶቻቸው እንዳይጣሱ ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ ስለሚያደርጉበት ሁኔታም ጥልቅ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ከጂ.አይ.ዜድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሰብዓዊ መብት ክትትል ማብራሪያ መጽሃፍ ታትሞ አገልግሎት ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን ለሁሉም ፍትሕ አካላት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህግ ትምህርት ቤቶች በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡