የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በሰራው የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ መነሻ ጥናት ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 05 ቀን 2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡
የመድረኩ አብይ አላማ በፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ መነሻ ጥናት ዙሪያ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባትን መፍጠር ሲሆን፤ የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ እንደ አገር የሌለን በመሆኑ የፍትሐብሔር ጉዳይ መነሻን የሚያሳይ፣ አሁን ያለበትን የሚያመለክት እንዲሁም ከዚህ አንጻር ወዴት መሄድ ይኖርብናል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አቅጣጫ የሚያመለክትና ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲ ማዘጋጀት ማስፈለጉ ተገልጿል፡፡
የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ መነሻ ጥናት ሲደረግ ከፍትሕ ሚኒስቴር፤ ከፍርድ ቤት እና ከጠበቆች የተወከሉ አባላት የተሳተፉበት የጥናት ቡድን ተመስርቶ ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ የተሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ጥናቱ በርካታ ጉዳዮችን ያካተተና በቀጣይነት ከሀገራዊ የልማት እቅዶች ጋር ተጣጥሞ ሊያሰራ የሚችል የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ ለማዘጋጀት እንዲያስችል ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ተወስቷል፡፡
የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ ቢወጣ እንደ ሀገር አንድ የጋራ የኢኮኖሚ ማህረሰብን ለመፍጠር፤ የተሟላ ንግድና ግብይትን ለማጽናት፤ የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ተጠቃሚነትን መፍጠር፤ ፍትሃዊ የሃብት ድልድልን እንዲኖር ከማድረግ፤ አማራጭ የፍትሕ መስጫ ስርዓት እንዲኖር ማስቻል፤ ተዓማኒነት ያለው የፍትሕ ስርዓትን የመፍጠር፤ በፍትሐብሔር ጉዳይ የሚኖር አለመግባባትን ቀልጣፋ፣ ተገማች እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የመፍታት፤ የመንግስትና የማህበረሰብን ጥቅም ሚዛናዊ የማድረግ፤ ማህበራዊ ፍትሕ የማስፈን፤ የህዝብን ጥቅም ማስከበር፤ ቀልጣፋና ዘመናዊ የፍትሕ ስርዓትን ማበጀት፣ ሕገ-መንግስታዊ የሆኑ የግለሰብ መብቶችን ማረጋገጥ፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶችን እንዲሁም ባህላዊና ሐይማኖታዊ ፍርድ ቤቶችን በአግባቡ ለመገልገል፣ በአጠቃላይ ተገቢው ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ የማስቻል ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በጥናት ቡድኑ በቀረበው ገለጻ ላይ ተመላክቷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ ቢወጣ የባለድርሻ አካላትን ጉልህ ሚና የበለጠ ለማሳየት፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፍትሐብሔር ፍትሕ አገልግሎት ሥርዓትን በተማሏ መልኩ ለመዘርጋት፣ ተቋማት ኀላፊነታቸውን እንዲያውቁ የማድረግ፣ በተቋማት መካከል የቴክኖሎጂ ትስስር እንዲኖርና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተቋማዊ በሆነ አሰራር ውስጥ እንዲካተት ማድረግ የሚቻልበትን አማራጭ የሚያስገኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ በመድረኩ የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ መነሻ ጥናት መነሻ ሐሳቦች፣ የጥናቱ ግኝቶች እና የጥናቱ ምክረ ሐሳቦች በተሟላ ሁኔታ ቀርበው በመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሐሳብና አስተያየቶች ከተሰጡና ለተነሱ ጉዳዮች ከመድረክ ማብራሪያ ከቀረበ በኋላ ጥናቱን መሰረት አድርጎ ፖሊሲውን የማርቀቅ ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር እና የፖሊሲው መውጣት የፍትሐብሔር ፍትሕ አስተዳደር ስርዓቱን እንደሚያሻሽለው የጋራ መግባባት ተፈጥሮና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ተመላክተው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡