በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን አስመልክቶ የዕውቅናና የትግበራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዕውቅናና የትግበራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ መድረክ ላይ የተገኙትን ሚኒስትሮች ፣አምባሳደሮች የዓለም ዓቀፍና የሀገር አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እና ተጋባዥ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ሁላችሁም እንደምታውቁት ረዥም በሆነ ሂደት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማዘጋጀት ብዙ ባለሙያዎች በተሳተፉበት ሂደት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቶ መጋቢት 9/2016 ዓ.ም ረቂቅ ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን አውስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አያይዘው እንደገለፁት የዚህ መርሀ ግብር አንዱ ዓላማ የፖሊሲውን መፅደቅ ለማብሰር እና በፖሊሲ መፅደቅ ሂደት ለተሳተፉ የቡድኑ አባላት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት መርሀ-ግብሩ መዘጋጀቱን ገልጸው ፖሊሲው መፅደቁን ተከትሎ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችን በተመለከተ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር ቴዎድሮስ ምሕረት በመድረክ መክፈቻ ንግግራቸው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ተቀብሎ ማፀደቅ በራሱ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ጉልህ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ጥሰቶቹን ተከትሎ የተፈጠሩ ቁስሎችን በሽግግር ፍትሕ ስልቶች አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፈወስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀው ፖሊሲው ግቡን መታ ሊባል የሚችለው ግን በፖሊሲው የተመላከቱ ስልቶች በተሟላ ሁኔታ ተፈፃሚነት ሲኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ምክትል ዳሬክተር ጄኔራል የሆኑት ወይዘሮ ቃልኪዳን ደረጀ እንዳሉት በአገራችን ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ስርኣትን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ አደራ ተቀብለው በግልና በቡድን ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተው፤ የውጥናችን ግብ የሆነው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በአገራችን ዕውን እንዲሆን ባደረግነው አስተዋፅኦ አገራችን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲኖራት ማድረግ ችለናል በዚህም እንኳን ደስ አለን ብለዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራሏ አያይዘውም ዛሬ የተዘጋጀውን የዕውቅናና የትግበራ ማስጀመሪያ መድረክ ለቀጣይ የጉዞ ምዕራፍ መሠረት ለመጣል የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን አስመልክቶ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ያለፈበትን ሂደት የሚያሳዩ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ ዌብሳይት መከፈቱ ተበስሯል፡፡