በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ህግ ትምህርት እና ስልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ከተለያዩ ሚኒስቴር መ/ቤቶች እና ከፌደራል የመንግስት ተቋማት ለተውጣጡ የሕግ ባለሙያዎች ሕግ ማርቀቅ በኢትዮጲያ እና የፌደራል አስተዳደር ሥነ- ስርዓት ሕግ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር በመቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ላይ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት ውስጥ በህግ ጉዳይ የፌደራል መንግስት አማካሪ ከመሆኑ በተጨማሪ ለመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች እና ሰራተኞች የሕግ ጉዳዮች ስልጠና መስጠት አንዱ በመሆኑ በዚህም መሰረት በየዓመቱ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በማካሄድ በተለዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠታቸው የተጠቆመ ሲሆን ይህም ርዕስ በፍላጎት ዳሰሳ የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ ሀገር ያልተማከለ ስርዓት ስለምንከተል እያንዳንዱ ሚኒስቴር መ/ቤት ሕግ የሚያመነጭና የሚያረቅ በመሆኑ ስልጠናው እውቀት እና ክህሎትን ለማዳበር ታስቦ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ስርዓት ሕግ የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መልኩ መሰጠት ያለበት መሆኑ በህገ መንግስቱ የተመላከተ በመሆኑ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ሲሰጡ እና መመሪያ ሲያወጡ ወጥ እና ግልፅ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው በአዋጅ ቁጥር 1183/12 የተቀመጠ ስለሆነ በዚህ ዙሪያ ለሚኒስቴር መ/ቤቶች እና ለፌደራል የመንግስት ተቋማት የሕግ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ስልጠናው ለሁለት ቀናት ሚቆይ ሲሆን በዛሬ ውሎው የሕግ ማርቀቅ ሥነ-ስርዓቶችና ስልቶች እንዲሁም ቴክኒካዊ ጉዳዮች፤ በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሚሳተፉ ዋና ዋና አካላት፤ ሕግ የማመንጨት (የማርቀቅ) ስልጣን በኢትዮጲያ ምን ይመስላል? የሚሉትና ከሕግ አረቃቀቅ ጋር የተያያዙ አጠቃላይ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን በቀጣይ የአስተዳደር ሥነ ስርዓት ሕግን በሚመለከት ሰፋ ያለ ገለፃ እና ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡