“ብዝኀነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ቃል ጷጉሜን 2 ቀን የሚከበረውን የኅብር ቀን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር፤የሰላም ሚኒስቴር፤የትምህርት ሚኒስቴር ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ባህልና ስፓርት ሚኒስቴር እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ በፓናል ዉይይት በማካሄድ አክብረዋል፡፡
በኃይማኖት አባቶች ጸሎትና ምርቃት የተጀመረው የፓናል ዉይይት ዋና ዓላማ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጽናት ስኬቶቻችንን ማስቀጠል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ” የጋራ ታሪክና ባህል ለብዝኃነት፤ ማኅበራዊ ዕሴቶች እና ሀብቶች በኢትዮጵያ እንዲሁም ሚዲያ ለአገራዊ ግንባታ ባለዉ ፋይዳ ” ላይ ትኩረት ባደረጉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ምሁራን ለታዳሚዎቹ የዉይይት መነሻ ሀሳቦችን አቅርበዋል፡፡
ከአንድነት ይልቅ ልዩነታችን ላይ ትኩረት ያደረገዉ የፖለቲካ ባህላችን አሁን ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚቀነቀነዉ የተሳሳተ የጥላቻ ትርክት ጋር ተዳምሮ ነባር ዕሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መምጣቸዉን ምሁራኑ ያስረዱ ሲሆን፣ የጋራ ታሪክን በወጣቱ ትዉልድ በማስረጽ እና ሚዲያን የሕብረ ብሄራዊ አንድነታችን ማጠናከሪያ በማድረግ እና ለዲሞክራሲ እና ሰላም ግንባታ ቁልፍ የሆኑ እሴቶቻችንን እዉቅና በመስጠት መሠረቱ የተስተካከለ ትዉልድን በመፍጠር አካታች እና አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት ኅብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባ በፓናል ዉይይቱ ላይ ተወስቷል፡፡
ሕብረ ብሄራዊነታችንን አጠናክረን የአድዋን ድል በጋራ እንዳበሰርነዉ እና የታላቁ ኅዳሴ ግድብን እንዳጠናቀቅነዉ ሁሉ የባሕር በራችንን ለማስመለስ አንድነታችንን ማጽናት ግድ የሚለን የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደምንገኝ በመድረኩ ተሳታፊዎች ተንጸባርቋል፡፡
በዉይይት መድረኩ ሚኒስትሮች፤ሚኒስትር ዲኤታዎች፤ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ መካከለኛ አመራሮች፤የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፤ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተሳትፈውበታል፡፡