በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት በመገኘት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የተገኙ ውጤቶች እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ለማሳካት የታቀዱ ግቦች ላይ ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሰራተኞች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በመድረኩ በ2017 በጀት ዓመት በታቀዱ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም በ2018 ለማሳካት የታቀዱ ስራዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የተያዙ ግቦችን ከማሳካት ረገድ አመርቂ ውጤት የተመዘገበ መሆኑን ይህም የሚያበረታታ እና በ2018 በጀት ዓመት ለታቀዱ ተግባራት እንደ ጥሩ መነሻ የሚወሰድ መሆኑን በተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡
በውይይት መድረኩ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት ባለፈው 2017 በጀት ዓመት በፍትሕ ዘርፍና በተቋም ደረጃ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን በማንሳት በ2018 በጀት ዓመት የተያዙ ግቦችን ለማሳካት እና በተሻለ ሁኔታ ለመፈፀም ሁሉም የጽ/ቤቱ አመራሮች እና ሠራተኞች በዕቅድ የተያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት መትጋት እንዳለባቸው እና ባለፈው በጀት ዓመት ያልተሳኩ ጉዳዮች ለማሳካት ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በቀጣይ ቀናት ከድሬዳዋ ፖሊስ ጋር በጋራ የሚሰሩ የምርመራ፣ የክስና ክርክር ተግባራትን በሚመለከት የአፈፃፀም ግምገማ የሚደረግ ይሆናል፡፡