የአማርኛ ቋንቋ ሞክሼ ሆሄያት በሕግ ሰነዶች ውስጥ ወጥ የሆነ የአጻጻፍ ሥርዓት እንዲኖራቸው እየተሰራ እንደሆነ ተገለፀ

Work Underway to Establish Uniform Writing System for Amharic Homophones in Legal Documents

የአማርኛ ቋንቋ ሞክሼ ሆሄያት በሕግ ሰነዶች ውስጥ በወጥነት አገልግሎት ላይ የሚውልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እና ከተለያዩ ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ምሁራን፣ በሕግ ማርቀቅ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እና ሌሎች በዘርፉ ልምድ ያላቸው ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የሕጎችን ጥራት ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሕግ ጥራት ማሻሻያ ስራዎች መካከ በሕግ ሰነዶች ውስጥ ሞክሼ የሆኑ የአማርኛ ፊደላት የሚጻፉበትን ወጥ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት አንዱ ነው። በዚህ መሰረ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል ማእከል የጋራ ትብብር የተከናወነው በሕግ ሰነዶች ውስጥ የአማርኛ ሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም መነሻ ጥናት ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በቀረበው ጥናት በሕግ ሰነዶች የአማርኛ ሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም ዘፈቀዳዊ እና ወጥነት የሌለው በመሆኑ በሕጎች ወጥነትና ጥራት ላይ ጉልህ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በረቂቅ ሕግ ዝግጅት ሂደት የሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም ወጥነት እንዲኖረው ለማድረግ የጥናቱን ግኝት መነሻ በማድረግ የተዘጋጀው ረቂቅ ማኑዋል ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ማኑዋሉ በሕግ ሰነድ ዝግጅት ሂደት ወጥነት ያለው የሞክሼ ሆሄያት አጻጻፍ ሥርዓት እንዲኖር፣ ፊደላቱ ለተገቢው ዓላማና ትርጉም እንዲውሉ ለማድረግ እንዲሁም በሕግ ሰነድ ውስጥ የሚስተዋለውን የሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም ዥንጉርጉርነት ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋዕጾ እንዳለው ተገልጿል።

ማኑዋሉ ከፍትሕ ሚኒስቴር በተጨማሪ ሌሎች ተቋማት የሕግ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ ሆሄያቱን ወጥነት ባለው መልኩ እንዲጠቀሙ እና ጥራት ያለው ሕግ እንዲያዘጋጁ እንደሚረዳ የተገለጸ ሲሆን የሕግ አርቃቂ ባለሙያዎችም ሞክሼ ሄሄያትን አጠቃቀም ተረድተው ወጥነትና ጥራት ያለው ሕግ ለማርቀቅ አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል።

በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ እና ረቂቅ ማኑዋል ላይ ተሳታፊዎች ውይይት አድርገውበታል፤ ረቂቅ ማኑዋሉን ለማሻሻል የሚያስችሉ ገንቢ አስተያየቶች/ግብዓቶች ተሰብስበዋል። በሌላ በኩል በሕግ ሰነዶች የሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀምን ወጥነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀው ማኑዋል በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ሞክሼ ሆሄያት ያሉበት ቃላት ሲጻፉ ትክክለኛውን አጻጻፍ የሚያመላክት ሥርዓት (Spell Checker) እንደሚዘጋጅ በመድረኩ ተገልጿል።

Tagged Under: act amharic amharic legal document amharic legal documents check court decree document Documents judge judicial judiciary law legal Legal Documents legislation lis one phone phones Policy proclamation Regulation statute system tribunal un uniform way work
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች