በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ፣ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ከሐምሌ 14 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና ለተቋሙ መካከለኛ አመራሮችና ዐቃብያነ ሕግ መስጠት ጀምሯል፡፡
የሥልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልክቸው ወርቁ እንዳሉት ÷ በኢኮኖሚ ወንጀሎች በተለይም ከታክስ እና ሸማቾች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የተወሰኑ ጉዳዮች ወደ ምድብ ጽሕፈት ቤት መውረዳቸውን አውስተው፤ወንጀሎችን እንዴት እንያዝ ? ከክስ ጀምሮ እንዴት ነው ልንመረምር የምንችለው?እንዴትስ ነው ማስረጃዎቻቸውን የምንመዝነው? ችሎት ላይ ክርክር ስናደርግ ምን ምን ነጥቦች ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን? የሚሉት በዋናነት በሥልጠናው የሚዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናው በአመራሮችና በዐቃቤያን ሕግ የሥልጠና ፍላጎት መነሻነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ወንጀሎች በምድብ ጽሕፈት ቤቶች እንዲታዩ በመውረዳቸው ምክንያት መዘጋጀቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በሥልጠናው ከኢኮኖሚ ወንጀሎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስመልክቶ አመራሮችና ዐቃቤያነ ሕግ የወንጀሉን ውስብስብነት በደንብ አውቀው፤ በትኩረት እንዲከታታሉ የሚያስችላቸው መሆኑን አውስተው ፤በሥልጠናው በሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሠልጣኞች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ተቋሙ እንደ ዋነኛ ምሰሶ ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ የተቋም ግንባታ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የተቋም ግንባታ ያለ ሰው የሚታሰብ አለመሆኑን ገልጸው፤ ሰው ላይ መሥራት መሠረታዊ ነገር ነው ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም ዳሬክቶሬቱ በየዓመቱ በሚያደረገው የሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ መሠረት ብዙ የሥልጠና ፍላጎት የታየባቸውን ርዕሶች እየለየና የሥልጠና ዕቅድ እያዘጋጀ ሥልጠና እየሰጠባቸው መሆኑን አውስውስተዋል::
በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ፣የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ያለ ደረሰኝ ግብይት፣በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ፣ሀሰተኛ ገንዘብ መያዝ /ማስቀመጥ፤ማቅረብ ፣የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2017 እና የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 እና ማሻሻያው1160/11 በሥልጠናው የሚዳሰሱ ይዘቶች መሆናቸው ተመላክቷል፡