የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ዓቅም በማጎልበት የወንጀል ፍትሕ ስርዓት ለማሻሻል ከአውሮፓ ህብረት በተደረገ የፕሮጀክት ድጋፍ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ሙያዊ ክህሎት ለማዳበር የሚያግዝ የሥልጠና መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሔደ::
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን በንግግራቸው ኮሚዩኒኬሽን ትጉህ፣ የፈጠራን አቅም የተላበሰ እና ሙያው የሚጠይቀውን የእውቀት እና ስነ-ምግባር ሁኔታ የሚያሟላ ሙያተኛ የሚፈልግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት የሪፎርም ስራዎችን አቅዶ ሲከውን እንደነበር ጠቁመው የሪፎርም ስራዎቹ ያመጡትን ለውጥ በማስቀጠል ሕዝቡ ከተቋሙ የሚጠብቀውን አይነት የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ሌሎች የፍትሕ ዘርፉን ተቋማት የሚያካትት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ታቅዶና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደተግባር ገብተዋል ፤ ፍትሕ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትን አሳትፎ አሁን ያለውን የፍትሕ ስረዓት ለመለወጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል ፤ በዋናነትም ማኅበረሰብ አቀፍ የግጭት አፈታት ስርዐትን ማጎልበት ቅድሚያ ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ማህበረሰቡ የፍትሕ ስርዐቱ ውስጥ ያላቸውን አይተኬ ሚና ተጠቅመው ለዕቅዱ መሳካት የበኩላቸውን መጫወት አለባቸው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ሥልጠናው የተቋማችሁን ገጽታ በመገንባት የራሳችሁን ሚና ከመጫወት ባሻገር በተቋማችሁና በህዝቡ እንዲሁም በተቋሙ በሰራተኞች እና አመራሮች መካከል የሚኖረው ግንኙነት የተሻለ እንዲሆን የሚያስችል ስራ መሥራት የሚያስችላችሁን ዕውቀት የሚያስጨብጥ ይሆናል በማለት ተናግረዋል ፡፡
ሥልጠናው በርከት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን አቶ ነጻነት ተስፋዬ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፣ ጋዜጠኛ አቶ ጌታቸው ሰናይ እንዲሁም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ሥልጠናውን ሰጥተዋል፡፡
በሥልጠናው ከፍትሕ ሚኒስቴር ፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ ከታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እና ከማረሚያ ቤት ኮሚሽን የመጡ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በሥልጠናው መቋጫ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እንዲህ ያሉ የባለሙያውን አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው ቀጣይነት ሊኖረው እደሚገባም ጠቁመዋል፡፡