ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም ለሰላም ሚኒስቴር የካውስል ማናጅመንት አባላት እና የቡድን መሪዎች የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሂሩት ዲሌቦ የዚህ ሥልጠና ዓላማ በአዋጁ ላይ ግልፅ የሆነ ግንዛቤ በመያዝ በመንግሥት አሰራሮች ላይ ግልፀኝነትን እና ተጠያቂነትን ማስፈን መሆኑን ተናግረዋል ።
ሥልጠናውን የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ሀወኒ ታደሰ የፍትሕ ሚኒስቴር አንዱ ተልዕኮ የሚወጡ የፌዴራል ህጎችን አፈፃፀም መከታተል መሆኑን ገልፀው የፌዴራል አስተዳደር ሥነ- ስርዓት አዋጅ ዓላማ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆኑን የሚደነግገውን ህገ-መንግስታዊ መርህ ማስተግበር ነው ብለዋል።
አዋጁ የአስተዳደር ተቋማት በዜጎች መብት ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት በሕግ እንዲመራ፣ ከሕግ ውጪ በሆነ ጊዜም ዜጎች መብታቸውን በፍርድ ሂደት የሚያስከብሩበት እና አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚያገኙበትን እድል መፍጠር መሆኑንም ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።
ሥልጠናው የፌደራል አስተዳደር ሥነ- ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ትርጉም፣ ዓላማ፣ ምን ምን ጉዳዮች እንደያዘ፣ በአዋጁ የተቀመጡ የመመሪያ አወጣጥ ሥነ-ስርዓቶች፣ የአስተዳደር ውሳኔ መርህ እና ሂደቶች እንዲሁም እነዚህን ሂደቶች በአግባቡ አለመተግበር የሚያስከትለው ውጤት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል።
ተሳታፊዎችም በቀረበው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ያላቸውን ጥያቄ እና አስተያየት አንስተው ውይይት ተደርጎበታል።